Fana: At a Speed of Life!

ለአዋሽ ወልዲያ ሀራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ለመገንባት ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 12 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአዋሽ – ወልዲያ ሀራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት የኃይል አቅርቦት የሚያገለግል የከፍተኛ ኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ስራ ለማከናወን የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ፡፡

ስምምነቱ ለባቡር ፕሮጀክቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል ባለ 230/132 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ ኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ነው።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ እና የቻይናው ፒንጋኦ ግሩፕ ኦቨርሲስ ማርኬቲንግ ዳይሬክተር ዣይ ያንቢን ተፈራርመዋል፡፡

የባቡር ፕሮጀክቱ ካለው ሃገራዊ ጠቀሜታ አኳያ የፕሮጀክቱ ግንባታ ስራ በተያዘለት የጊዜ መርሃ ግብር ጥራቱን ጠብቆ መጠናቀቅ እንዳለበት ዋና ስራ አስፈፃሚው አሳስበዋል፡፡

ለፕሮጀክቱ ግንባታ የመስመር ዝርጋታውን ለማጠናቀቅ ብቻ 11 ነጥብ 5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ተመድቧል፡፡

መንግስት የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በሰጠው ትኩረት መሰረት የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጪ በኢትዮጵያ መንግስት እንዲሸፈን መደረጉን ዋና ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል፡፡

የቻይናው ፒንጋኦ ግሩፕ ኦቨርሲስ ማርኬቲንግ ዳይሬክተር ዣይ በበኩላቸው የፕሮጀክቱን አስፈላጊነት ስለተገነዘብን ፕሮጀክቱን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ጥራቱን ጠብቆ እንዲጠናቀቅ በትኩረት እንሰራለን ብለዋል፡፡

206 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚኖረው የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ግንባታ በ12 ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የአዋሽ – ወልዲያ ሀራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት የግንባታ ስራ ተጠናቆ የኃይል አቅርቦት በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.