Fana: At a Speed of Life!

ለአዕምሯዊ ንብረት መብቶች መከበር መገናኛ ብዙሃን የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 25፣ 2013(ኤፍ.ቢ.ሲ) ለአዕምሯዊ ንብረት መብቶች መከበር መገናኛ ብዙሃን ለማህበረሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር የድርሻቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ጠየቀ።

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት በንግድ ምልክት፣ በፓተንት፣ በቅጅና ተዛማጅ መብቶች ምንነት ላይ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰጥቷል።

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳሉ ሞሲሳ÷ በተመዘገቡ የአእምሯዊ ፈጠራ መብቶች ላይ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የመብት ጥሰት እየተፈፀመ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም የፈጠራ ባለቤቶች ህዝብን ሲያገለግሉ ቆይተው ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም ሳያገኙ ለችግር እየተዳረጉ እንዳሉ ገልጸዋል።

የሰዎችን የአዕምሮ ንብረት ያለፈቃድ መጠቀም ወንጀል መሆኑንና ተጠያቂነትን እንደሚያመጣ ህብረተሰቡ አውቆ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ በማስገንዘብ መገናኛ ብዙሃን የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል።

የአእምሯዊ ንብረት እውቀትና ግንዛቤን በማህበረሰቡ ውስጥ በማስረጽ በኩልም መሰራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ጽህፈት ቤቱ በዋናነት ለሰው ልጅ የአእምሮ ፈጠራ ውጤቶች የጥበቃ ስራን እንሚያከናውን የገለጹት አቶ እንዳሉ÷ የፈጠራው ባለቤቶች መብቶቻቸውን አስከብረው ተጠቃሚ የሚሆኑበት ስርአት መዘርጋቱንም ጠቁመዋል።

አያይዘውም ሀገር፣ ማህበረሰቡና ባለሙያዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለመብቶቻቸው ተመጣጣኝ የሆነ ክፍያ በስራዎቻቸው ተሰብስቦ ለባለመብቶች የሮያሊቲ ክፍያ እንዲከፈል ጥረት እየተደረገ ይገኛልም ብለዋል።

ተቋማት ለሚገዟቸው የፈጠራ ምርቶች የሚያደርጓቸውን ውሎች አስመልክቶም ጽህፈት ቤቱ የሙያና የምክር አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት የኮፒራይት የሥራ ሂደት ኃላፊ አቶ ናስር ኑሩ በበኩላቸው÷ በአንዳንድ የሬድዮና የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ያለባለቤቶቹ ፈቃድ ሥራዎቻቸው ጥቅም ላይ ሲውሉ እየታየ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ችግሩን ለመከላከል ባለመብቶች በማህበር ተደራጅተው ጥቅማቸውን እንዲያስከብሩ ለማድረግ ሥራዎች መጀመራቸውን ጠቁመዋል።

በህብረተሰቡና በባለሙያው በኩል ያለውን ክፍተት ለመሙላትም መሰል የግንዛቤ ማስጨበጫዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.