Fana: At a Speed of Life!

ለአይነ ስውራን ዘመናዊ በትር (ኬን) ተሰራ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)ተመራማሪዎች ለዓይነ ስውራን በእንቅስቃሴ የሚያግዝ ዘመናዊ በትር ወይም ኬን ሰርተው አቀረቡ፡፡

በተለምዶ ነጩ ምርኩዝ በመባል የሚታወቀው ይህ አይነስውራን ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ የሚጠቀሙበት ዘንግ ተጠቃሚዎቹ የሚኖራቸውን እንቅስቃሴ የተሻለ ቀላል እንዲሆን ያደርገዋል፡፡

መደበኛው ዘንግ ከመሬት ጋር ሲጋጭ የሚኖረውን ድምጽ በመከተል አንድ አይነስውር በቀላሉ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ይችላል፡፡

ሳንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ይህንን መደበኛ ዘንግ በማሻሻል አይነ ስውራን ከደህንነት ስጋት ነጻ ሆነው እንደፈለጉ እንዲንቀሳቀሱ በሚያስችል መልክ የሮቦት ቴክኖሎጂ አክሎበት ማቅረቡ ተነግሯል፡፡

ከራስ ነድ መኪኖች ቴክኖሎጂ ጋር ተጣምሮ የተሰራው ይህ ዘንግ በ400 ዶላር የቀረበ ሲሆን÷ ተጠቃሚዎች እንደሚኖሩበትና እንደሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ምቹ የሆነ ድጋፍን የሚሰጥ ነው ተብሏል፡፡

ስማርት ዘንጉ በመንገድ ላይ ወይም በየትኛውም አካባቢ የሚኖሩ እንቅፋቶችን በመለየት በቤት ውስጥም ሆነ ከቤት ውጭ ለመንቀሳቀስ ምቹ የሆኑ ቦታዎችን በመምረጥ መጓዝ የሚያስችል ነው፡፡

በዘርፉ ሌሎች ሴንሰር የተገጠመላቸው መሪ ዘንጎች ያሉ ቢሆንም ከአጠቃላይ ክብደታቸው እና ከሚያወጡት ዋጋ አንጻር ተፈላጊነታቸው አነስተኛ ነው፡፡

በሌላ በኩል ከቴክኖሎጂ አንጻር እጥረት ያለባቸው በመሆኑ ማለትም ሴንሰሩ ከተጠቃሚው ፊት ለፊት ያለን ነገር ብቻ የሚያሳውቅ በመሆኑ ይህ ተሻሽሎ የቀረበው መሪ ዘንግ ተመራጭ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡

ከዚህ በፊት የነበረው ሴንሰር የተገጠመለት መሪ ዘንግ ወይም ኬን 50 ፓውንድ የሚመዝንና እስከ 6 ሺህ ዶላር የሚያወጣ ሲሆን÷ ይሄኛው ግን ሶስት ፓውንድ የሚመዝንና 400 ዶላር ብቻ የተቆረጠለት ነው፡፡

ተመራማሪዎቹ አሻሽለው ያቀረቡት መሪ ዘንግ በአለማችን ላሉ ከ250 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዓይነ ስውራን ጥቅም ይሰጣል ብለው ተስፋ ማድረጋቸውን ቴክ-ኤክስፕሎርን ጠቅሶ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስነብቧል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.