Fana: At a Speed of Life!

ለወራት ከአገልግሎት ውጪ ሆኖ የቆየው የተከዜ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ዛሬ ሥራ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ለወራት ከአገልግሎት ውጪ ሆኖ የቆየው የተከዜ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ዛሬ ሥራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አስታወቀ።
የኃይል ማመንጫ ጣቢያው ከብሔራዊ የኃይል ቋት (ግሪድ) ጋር የሚገናኝበት መስመር በመቋረጡ ምክንያት ኃይል ማመንጨት አቁሞ እንደነበር ይታወሳል።
ከተከዜ- መቀሌ በተዘረጋው የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ ሲደረግ የነበረው ጥገና በመጠናቀቁ ዛሬ ቀን ከ 7 ሰዓት ጀምሮ በጊዜያዊነት ከሲስተም ጋር ሳይገናኝ ራሱን በራሱ እየተቆጣጠረ ኃይል መስጠት መጀመሩ ተገልጿል።
በአሁኑ ሰዓት ጣቢያው ካሉት አራት ዩኒቶች መካከል በሁለት ዩኒቶች እስከ 108 ሜጋ ዋት ድረስ ኃይል እየሰጠ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ካለፈው ሐሙስ ከሰዓት ጀምሮ በትግራይ ተቋርጦ የነበረው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዛሬ ከተከዜ ኃይል ማመንጫወደ መቀሌ የሚሄደው መስመር ተጠግኖ የተከዜ ኃይል ማመንጫ ስራ በመጀመሩ ዳግም አገልግሎት ማግኘት ጀምሯል።
ቀደም ሲል ከአላማጣ መኾኒ አሸጎዳ መቀሌ የሚሄደው መስመር ላይ ባጋጠመ ችግር ምክንያት የትግራይ ክልል ኤሌክትሪክ ተቋርጦ እንደነበረ ሀይሉ የገለፀው።
በትግራይ በተካሄደውን የህግ ማስከበር ተከትሎ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰ ሲሆን የተከዜ ግድብ ደግሞ መንግስት በአውሮፕላን ደብድቦ አፍርሶታል ተብሎ የሀሰት ወሬ ተናፍሶ እንደነበረም አስታውሷል።
በወቅቱም በግድቡ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳልደረሰ ገልፆ እንደነበረም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አስታውሷል።
የተከዜ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በአራት ዩኒቶች 300 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም እንዲኖረው ተደርጎ የተገነባ ባለ ጥምር ቅስት የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ነው።

መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.