Fana: At a Speed of Life!

ለድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ድጋፍና ትብብር እንዲደርግ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ወጭና ገቢ ንግድ ሎጀስቲክስ አገልግሎት ላይ ትልቁን ሚና እየተወጡ ለሚገኙ የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ህብረተሰቡ ድጋፍና ትብብር እንዲያደርግ ተጠየቀ።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በመከሰቱና በተለይ ደግሞ በአጎራባች አገሮች ቫይረሱ እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ ድንበር ተሻጋሪ የጭነት አሽከርካሪዎች ላይ መገለል እየደረሰባቸው መሆኑ እየተነገረ ነው።

በዚህም የትራንስፖርት ባለስልጣን ከኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር በድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ላይ የሚስተዋለውን የመገለል ችግር ለመፍታት የግንዛቤ ስራ ማከናወን ጀምሯል።

የግንዛቤ መፍጠር ስራው ከድሬዳዋ የተጀመረ ሲሆን በአይሻ ደወሌ መስመር እስከ ጅቡቲ በሚዘልቀው መስመር ላይ በቀጣዮቹ ቀናት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑም ታውቋል።

በቅስቀሳውም በአገሪቱ በወጭና ገቢ ሎጀስቲክስ አገልግሎት የተሰማሩ የጭነት አጓጓዥ አሽከርካሪዎችን ማህበረሰቡ ክብር በመስጠትና በማገዝ እንዲተባበራቸው ተጠይቋል።

ድንበር እያቋረጡ የግብርና፣ ኢንዱስትሪና የግንባታ ግብዓቶችን በማመላለስ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በማንቀሳቀስ የአሽከርካሪዎቹ ሚና ትልቅ መሆኑም ተመላክቷል።

አስከፊውን ጊዜ በትብብርና በመተጋገዝ ማለፍ እንደሚገባም ተጠቁሟል።

በተጨማሪም ባለፈው ዓመት ተገንብቶት አገለግሎት መስጠት የጀመረው የድሬዳዋ-አይሻ-ደወሌ የፍጥነት መንገድ የአዋሽ-ሚሌ-ሰመራ-ጋላፊ መንገድን በመተካት እንደ አማራጭ መንገድ ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.