Fana: At a Speed of Life!

ለግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኃይል ለማቅረብ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ለግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

ለምርቃት ዝግጁ ለሆነው ለቡሬ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ሁለት አማራጮች ተይዘው ጥናት ሲካሔድባቸው መቆየቱን የተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ገልፀዋል ፡፡

ለፓርኩ ኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ከባህርዳር ማከፋፈያ ጣቢያ በዳንግላ- ቡሬ በኩል 69 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ባለ 132 ኪሎ ቮልት መስመር እንዲሁም ከደብረ-ማርቆስ ማከፋፈያ ጣቢያ ወደ ፓርኩ የሚሄድ 92 ኪሎ ሜትር ባለ 230 ኪሎ ቮልት መስመር የመዘርጋት አማራጮች ተለይተው የቴክኒክና የፋይናንስ ትንተና እንደተካሄደባቸው ተናግረዋል፡፡

በተደረገው የቴክኒክና የፋይናንስ ትንተና መሠረት ከባህርዳር-ዳንግላ እንዲመጣ የታሰበው የማስተላለፊያ መስመር ባለ 132 ኪሎ ቮልት በመሆኑ ፓርኩ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር የኃይል መዋዠቅ ሊያጋጥም እንደሚችል አመልክቷል፡፡

በዚህም ምክንያት ከደብረ-ማርቆስ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የማከፋፈያ ጣቢያ ጀምሮ እስከ ቡሬ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ የኢንዱስትሪ ፓርክ ድረስ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር እና የማከፋፈያ ጣቢያ ለመገንባት መታቀዱን ነው አቶ ሞገስ ያብራሩት፡፡

ፕሮጀክቱን ለማከናወን ዓለም አቀፍ ጨረታ እንዲወጣ ተደርጓል ያሉት ኃላፊው የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሩን እና የማከፋፈያ ጣቢያውን ገንብተው ለማስረከብ ብቃት ያላቸው ሥራ ተቋራጮች እስከ የካቲት 5 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ክፍት በተደረገው ጨረታ ላይ እየተሳተፉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የወሰን ማስከበር ጉዳይ ለፕሮጀክት ግንባታ መጓተት ምክንያት እንዳይሆን ከወዲሁ ሥራዎች ተጀምረዋል ነው ያሉት፡፡

ፕሮጀክቱ ቀደም ሲል በመንግሥትና የግል አጋርነት ይገነባሉ ተብለው ከተለዩት መካከል አንዱ እንደነበር የጠቆሙት ኃላፊው በተለያዩ ምክንያቶች ዕውን ሊሆን አለመቻሉን ገልፀዋል፡፡

ለቡሬ፣ ለቡልቡላ፣ ለባከርና ለይርጋለም የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኃይል ለማቅረብ አሸናፊው ተቋራጭ ከተለየ በኋላ ፕሮጀክቱን በ12 ወራት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.