Fana: At a Speed of Life!

ለመዲናዋ ወጣቶች ከ200 ሺህ በላይ የሥራ ዕድል ተመቻችቷል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ የሥራ ዕድል ፈጠራና ልማት ኢንተርፕራይዝ ባለፉት አስር ወራት ብቻ ከ200 ሺህ ለሚልቁ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን አስታወቀ።

የኢንተርፕራይዙ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚኪያስ ሙሉጌታ እንደገለጹት የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው 229 ሺህ 46 ዜጎች መካከል 82 ከመቶ በላይ ወጣቶች ሲሆኑ፣ 9 ነጥብ 5 የሚሆኑት አዲስ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሩቋን ናቸው።

የኢንተርፕራይዙ የአስር ወራት ክንውንም በእቅድ ከተያዘው 110 ከመቶ እንደሆነም አመልክተዋል።

የሥራ ዕድል የተፈጠረባቸው የሥራ ዘርፎችም ማኑፋክቸሪንግ፣ ኮንስትራክሽን፣ የከተማ ግብርና፣ ንግድ፣ የአገልግሎት ዘርፍ እና የሥራ ቅጥር መሆናቸውንም አቶ ሚኪያስ ጠቁመዋል።

የሥራ ዕደሉ ከተመቻቸላቸው ውስጥ ከ52 ሺህ ለሚልቁት ሥራ ፈላጊዎች ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር በመተባበር በተለያዩ የሙያ መስኮች ስልጠና መሰጠቱንም አስረድተዋል።

በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ 18 ሺህ 100፣ በኮንስትራክሽን 18 ሺህ 436፣ በከተማ ግብርና 6 ሺህ 803፣ በአገልግሎት ዘርፍ 43 ሺህ 862፣ በንግድ 31 ሺህ 944 እንዲሁም በቅጥር 107 ሺህ 459 የሥራ ፈላጊዎቹ ወደ ሥራ ገብተዋል።

ኢንተርፕራይዙ ከዚህ በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ መጨረሻ 219 ሺህ 386 ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሥራ ዘርፉንና የሥራ አጡን በመለየትና በአንድ ቋት የመመዝገብ ሥራ መከናወኑንም አቶ ሚኪያስ አስረድተዋል።

ከነዚህ ሥራ ፈላጊዎች መካከል 119 ሺህ 391 ወንዶች፣ 99 ሺህ 993 ሴቶች ሲሆኑ፤ 78 ከመቶው  ወጣቶች ናቸው።

የስራ እድል ተጠቃሚዎቹ በበኩላቸው፥ በተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንደሆኑ በመግለፅ፤ የሥራ ዕድል ተጠቃሚዎቹ ወጣቱ ሥራ ሳይንቅ በመደራጀት መንግሥት በሚፈጥረው የሥራ ዕድል እንዲጠቀም ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.