Fana: At a Speed of Life!

ለ200 ታማኝ ግብር ከፋዮች እውቅና ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለ200 ታማኝ የፌዴራል ግብር ከፋዮች በዛሬው እለት እውቅና ተሰጠ።

ሁለተኛ ዙር የፌዴራል ግብር ከፋዮች  የእውቅና ስነስርዓት በዛሬው እለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት ተካሂዷል።

በአንድነት ፓርክ የተከናወነው ይህ መርሐ ግብር፣ ተመዝግበው የአሠራር ሂደታቸውን በተጠያቂነት ላከናወኑ እና ትኩረት ሰጥተው በወቅቱ ግብር ለከፈሉ 200 የንግድ አካላት እውቅና የተሰጠበት ነው።

በሶስት ደረጃ በተሰጠ በዚህ የእውቅና ሽልማት በአጠቃላይ 200 የፌደራል ግብር ከፋዮች እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

በዚህም ከግብር ከፋዮቹ 20 በፕላቲኒየም፣ 60 በወርቅና 120 በብር ደረጃ ተሸልመዋል።

በእውቅና አሰጣጥ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፥ “በታማኝነት ግብር የሚከፍሉ የሀገር ጀግኖች ናቸው፤ ነገር ግን፣ ታማኝ ግብር ከፋዮች ተብለው ዛሬ የሚሸለሙት 200 ብቻ ሳይሆኑ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ መሆን ነበረባቸው” ብለዋል።

“ከእናት መቀነትና ከሀገር ግብር መዝረፍ የመጨረሻው ውርደት ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ ግብር ከፋዮች በታማኝነት ግብር የሚከፍሉትን ያህል ሌብነትንም እንዲዋጉም ጥሪ አቅርበዋል።

ሙስና የሚጠይቁትን እጅ ከፈንጅ የሚያስዙ ግብር ከፋዮች ግብር እንዲቀነስላቸው የሚያደርግ አሰራር እንዲዘረጋ ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለታማኝ ግብር ከፋዮች በመንግስት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ቅድሚያ የሚያሰጣቸው አሰራር እንዲዘረጋም መመሪያ ሰጥተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.