Fana: At a Speed of Life!

መሰረታዊ የንግድ እቃዎችን በተገቢው መንገድ ለተጠቃሚው አለማድረስ በወንጀል ሕግ ተጠያቂ ያደርጋል – ፍትሕ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መሰረታዊ የሆኑና እጥረት እንዳለባቸው የተገለጹ የንግድ እቃዎችን በተገቢው መንገድ ለተጠቃሚው አለማድረስ በወንጀል ሕግ ተጠያቂ የሚያደርግ መሆኑን የፍትሕ ሚኒስቴር ገለጸ።
የንግድ እቃዎችን መደበቅ ወይም በሕገ-ወጥ መንገድ ማከማቸት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እሥራት የሚያስቀጣ ሲሆን ፥ መንግሥት ይህን ድርጊት የፈጸሙ ግለሰቦች ላይ እርምጃ መውሰዱን ሲገልጽ ቆይቷል።
በዚህ ተገቢ ያልሆነ የንግድ አካሄድ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በፍትሕ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ከፍተኛ ዐቃቤ ሕግ ታምራት አሳዬ ፥ መሰረታዊ የሆኑና እጥረት ያለባቸውን የንግድ እቃዎች ሥርጭት ማስተጓጎል በሕግ የሚያስጠይቅ ተግባር ነው ብለዋል።
በተለይም አከፋፋዩም ሆነ ቸርቻሪው የንግድ እቃዎችን በተገቢው መንገድ ለተጠቃሚው ካላደረሱ የወንጀል ሕጉ ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸውም ነው የተናገሩት።
ሕገ-ወጥ ድርጊቱ በወንጀል ሕጉ ብቻ ሳይሆን በፍትሐ ብሔር ሕጉም የሚያስጠይቅ ሲሆን ፥ የእሥራትና የገንዘብ ቅጣትን ጨምሮ የነጋዴውን ንብረትም ለመውረስ የሚያስችል አንቀጽን እንደያዘ አንስተዋል፡፡
ነጋዴው በዚሁ ተግባር ላይ መሳተፉ ከተረጋገጠ እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እሥራት የሚቀጣ ሲሆን ፥ ከዓመታዊ ሽያጩም ከአምስት እስከ ሰባት በመቶ ቅጣት እንደሚጣልበትም ነው ያስረዱት።
በተለይም እጥረት ያለባቸው የፍጆታ እቃዎች እንደ ስኳር፣ ዘይት፣ ስንዴ፣ የስንዴ ዱቄት እና ነዳጅን መደበቅ፣ ማከማቸትና ከመደበኛ ሥርጭት መስመር ውጭ እንዲተላለፉ ማድረግ ያስቀጣል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት እነዚህን የንግድ እቃዎች ከውጭ የሚያስገቡም ሆነ ሀገር ውስጥ የሚያከፋፍሉ አካላት በተፈቀደላቸው የሥርጭት መስመር ካልሰሩ ከተጠያቂነት እንደማይድኑ አመላክተዋል።
ነዳጅን ጨምሮ በመንግሥት ድጎማ የሚደረግባቸውም ሆነ የማይደረግባቸውን የንግድ እቃዎችን ማከማቸት፣ መደበቅና የሥርጭት መስመርን ማስተጓጎል ሕገወጥ ተግባር መሆኑንም ነው ያነሱት።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.