Fana: At a Speed of Life!

መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች “ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክትን በተመለከተ ገለጻ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች “ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክትን በተመለከተ ገለጻ ተደረገ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ባደረጉት ንግግር በቅርቡ እውን የሆነው የሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክት በብዙ መልኩ የዲፕሎማቲክ መቀመጫ የሆነችውን አዲስ አበባ ገፅታ የቀየረ መሆኑን አንስተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሃሳብ አፍላቂነት የሚጀመሩት አዳዲሶቹ የገበታ ለሀገር አካል የሆኑ ፕሮጀክቶችም ተመሳሳይ ግብ ያላቸው፣ ከውበት አልፈው የስራ እድል የሚፈጥሩ እና ለአረንጓዴ ኢኮኖሚም የራሳቸው ሚና የሚኖራቸው ናቸው ነው ብለዋል፡፡
ስለፕሮጀክቶቹ ጥቅም በመገንዘብ በሚመቻቸው መንገዶች ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉም አቶ ገዱ ጥሪ አቅርበዋል ፡፡

በመርሃ ግብሩ ስለፕሮጀክቶቹ አጠቃላይ ዝርዝር ፍላጎትና ተግባራዊነት የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ሚኒስትር ዶክተር አብረሃም በላይ እና የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

አንባሳደሮቹም የፕሮጀክቶቹ ፋይናንስን በተመለከተ፣ የአካባቢውን ማህበረሰብ ለመጥቀም ምን ያክል ሊሰራበት ታስቧል የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል።

ገለጻውን ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እንደገለፁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ‘’የገበታ ለሀገር’’ ፕሮጀክትን ለማሳካት እንቅሰቃሴ ጀምሯል።
እስከዛሬ ባለው እንቅስቃሴም በመስሪያ ቤቱ ውስጥ ‘’የገበታ ለሀገር’’ ፕሮጀክት የውጭ ሀብት አሰባሳቢ ንኡስ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን አምባሳደር ብርቱካን ተናግረዋል።
በመጨረሻም ‘’የገበታ ለሀገር’’ ፕሮጀክትን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ለማሳካት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሚዲያዎች ጋር የሚኖረውን ቀጣይ አንቅስቃሴ በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለጋዜጠኞች ተጨማሪ ገለጻና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በሀብታሙ ተ/ስላሴ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.