Fana: At a Speed of Life!

መንግስትና የሀይማኖት ተቋማት በሀገር አንድነትና ሰላም ላይ በጋራ መስራት እንዳለባቸው ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መንግስትና የሀይማኖት ተቋማት በሀገር አንድነት እና ሰላም ላይ በጋራ የተጠናከረ ስራ መስራት እንዳለባቸው ተጠቆመ።
 
የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ 12ኛ መደበኛ ጉባኤውን በዛሬው እለት በማካሄድ ላይ ይገኛል።
 
በጉባዔው ላይም የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እና የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዲሁም የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።
 
ጉባኤውንም በሀይማኖት አባቶቹ በፀሎትና እና ቡራኬ ያስጀመሩት ሲሆን፥ በቅርቡ በሀገሪቱ በተከሰተ ግጭት ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች የህሊና ፀሎት አድርገዋል።
 
በጉባዔው መክፈቻ ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፥ የሀይማኖት አባቶች በመተባበር እና በመተጋገዝ ለሀገር ሰላም እና አንድነት ለሚሰሩት ስራ መንግስት ከጎናቸው መሆኑንአንስተዋል።
 
“ሀገር ሰላም እንዳትሆን የማይፈልጉ ሀይሎች የከፋ ጉዳት ለማድረስ ብዙ ሰርተዋል አሁንም ይህንን ጠንክረን ማምከን እና እስከመጨረሻው ማሽከፍ ይግባናል ይህ ካልሆነ ግን ብዙ ነገር ከእጃችን ሊወጣ ይችላል” ነው ያሉት ወይዘሮ ሙፈሪያት።
 
ህግን በማሰከበር ሂደት መንግስት የጎላ ድርሻ አለው ያሉ ሲሆን፥ ሆኖም ግን ህግን የማሰከበር ስራ ልቦናን ከማቅናት ጋር አብሮ ካልሄደ ከንቱ ልፉት መሆኑን ነው ያነሱት።
 
በመሆኑም የሀይማኖት አባቶች እና ተቋማት በህብረተሰቡ የዋሉ እና ያደሩ ችግሮችን በሰለጠነ አስተሳሰብ እና ልቦናን በማቅናት የጎላ ድርሻ እንዳላቸወም አስገንዝበዋል።
 
በመሆኑም የሀይማኖት አባቶቾ እና ተቋማት ምእመናን በሀሳብ በመግባባት፤ በፍቅር እና በሰላም እንዲኖሩ መምከር እና መገሰፅ አለባቸው ብለዋል።
 
የጤና ሚኒሰትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው፥ የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ከተከሰተ ጀምሮ የሀይማኖት አባቶች በየእምነት ተቋሞቻቸው ምእመናንን በማስተባበር፣ በማስተማርና በመምከር የቫይረሱ ስርጭት እንዳይስፋፋ ሲሰሩ መቆየታቸውን አንስተዋል።
 
የሀይማኖት አባቶች ምእመናንን በመምከር እና በየእምነት ተቋማቸው ጾሎት በማድረግ ለካናወኑት በጎ ስራም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
 
አሁንም በቫይረሱ የሚያዙ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የሀይማኖት አባቶች ምእመናንን በማሰተማርና በመምከር እንዲሁም በመፀለይ የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
 
በዛሬው እለት መካሄድ የጀመረው ጉባኤው ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይና አጠቃላይ የበጀት ዓመቱ አፈጻጸምን የሚገመግም ይሆናል።
 
በመጨረሻም በ“አረጓንዴ አሻራ” መርሃ ግብር የችግኝ ተከላ በማካሄድ ጉባዔው እንደሚያጠናቅቅ ይጠበቃል።
 
በሲሳይ ጌትነት
 
#FBC
 
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.