Fana: At a Speed of Life!

መንግስት አሸባሪውን ህወሓት ይዟቸው ከነበሩ አካባቢዎች በማስወጣት ወረራውን መቀልበስ ችሏል – ቢለኔ ስዩም

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት አሸባሪውን ህወሓት ይዟቸው ከነበረሩ አካባቢዎች በማስወጣት ወረራውን መቀልበስ መቻሉን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ዓለም አቀፍ ግንኙነትና ሚዲያ ዘርፍ ሃላፊ ቢለኔ ስዩም ገለጹ፡፡

ሃላፊዋ በዛሬው እለት መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የውጭ መገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም አሸባሪው ቡድን በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና ጥምር ኃይሉ ሽንፈቱን ተከናንቦ ከያዘው አካባቢ ከመውጣቱና አካባቢውን ከመልቀቁ በፊት መጠነ ሰፊ ውድመት እና ጭፍጨፋ እንደፈጸመ ለማወቅ ተችሏል ብለዋል ሃላፊዋ፡፡

ቡድኑ የጤና እና የትምህርት ተቋማትን፣ የሃይማኖት እና የባህል ማዕከላትን እንዲሁም የኮምቦልቻ የኢንዱስትሪ ፓርክ ላይ ዘርፋና ውድመት ፈጽሟል፤ የህዝብ መረጃዎችንም አውድሟል ብለዋል፡፡

መንግስት አሸባሪው ህወሓት ይዟቸው የነበሩ አካባቢዎችን ካስለቀቀ በኋላ መልሶ ለማቋቋም እና የወደሙትን ተቋማት በተቻለ መጠን ጠግኖ ወደ ስራ ለማስገባት በማስተባበር እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

የሰብዓዊ መብትን በተመለከተም የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በጥምረት የሰሩትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርት ከእነ ክፍተቶቹ ተቀብሎ የተሰጡትን ምክረ ሃሳቦች እንደሚተገብር አስታውቀዋል፡፡

አያይዘውም መንግስት የሰብአዊ መብት ሪፖርቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተፈጸሙባቸውን አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ሳይሆን በከፊል የዳሰሰ ነው ብሎ እንደሚያምንና ይህንንም በወቅቱ ሪፖርቱን ላቀረቡ አካላት ገልጿል ነው ያሉት ሃላፊዋ፡፡

ከዚህ ባለፈም መንግስት ለ2ኛ ጊዜ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ በሌላ አካል ይመርመር የሚለውን ሃሳብ እንዳልተቀበለው ጠቅሰው፥ የአውሮፓ ኅብረት አካላት የሚፈልጉትን የፖለቲካ ፍላጎት በተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኩል ለማስፈጸም ካልሆነ በስተቀር የቀደመውን ምርመራ ላለመቀበል ምክንያት የላቸውም ብሎ እንደሚያምንም አስረድተዋል።

ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ውይይትን በተመለከተም መንግስት በገለልተኛ አካላት የውይይት መድረክ ለማዘጋጀት ቁርጠኛ መሆኑን ነው የገለጹት።

መንግስት በውይይቱ መካፈል ያለባቸውን አካላትን በመለየት፣ የውይይት አጀንዳ በመቅረጽ እና ውይይቱን ለማካሄድ የሚያስችሉ ስራዎች እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ጋር በተያያዘም መንግስት ለአማራ፣ አፋር እና ትግራይ ክልሎች የምግብ አቅርቦት ማሰራጨቱን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በሰሜን ወሎ ዞን ለወልዲያ፣ ቆቦ፣ መርሳ፣ በሰሜን ሸዋ ለአጣዬ፣ ኤፍራታ፣ አንጾኪያ፣ ሸዋ ሮቢት፣ እና መንዝጌራ ወረዳዎች እንዲሁም በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ለባቲ፣ አርጡም ፉርሲ፣ ደዌ ሐሮዋ፣ ጂሌ ጥሙጋ እና በደዌ ጨፋ ወረዳዎች በተጨማሪም ለጋሸና፣ ላሊበላ፣ ዋድላ እና ለላስታ ወረዳዎች የምግብ አቅርቦት እንዲሰራጭ አድርጓል ነው ያሉት፡፡

በአፋር ክልል ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ አቅርቦት በማስፈለጉ እና ከ400 ሺህ በላይ ዜጎች ከአካባቢያቸው በመፈናቀላቸው ለ21 ወረዳዎች እርዳታ መቅረቡን አስረድተዋል፡፡

በትግራይ ክልልም 225 የጭነት መኪኖች የእርዳታ አቅርቦት ይዘው ወደ ክልሉ መግባታቸውን አስረድተዋል፡፡

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.