Fana: At a Speed of Life!

መንግስት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሚወሰዱ አዳዲስ እርምጃዎችን ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 18 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኮቪድ-19ን ለመከላከል ከተቋቋመው ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተውጣጣ ኮሚቴ ጋር በኢንተርኔት አማካኝነት ያለውን የክንውን ሁኔታ እና ተጨማሪ መመሪያዎች እንዲሁም ኮቪድ-19ን ለመከላከል እና ስርጭቱን ለመግታት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን አስመልክቶ ውይይት አድርገዋል።
 
እስከ ዛሬ መጋቢት 18፣ 2012 ድረስ አጠቃላይ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 16 በመጨመሩ፣ ቫይረሱ በፍጥነት እየተዛመተ እንዳይሄድ ለመግታት ሲባል በቂ የመከላከል ሥራዎች መሠራታቸውን ለማረጋገጥ፣ የፌደራል መንግሥት በስፋት የቅድመ-ጥንቃቄ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ ተመልክተዋል።
 
ከውይይቱ በኋላ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚከተሉትን ተጨማሪ ቁልፍ እርምጃዎች ይፋ ያደረጉ ሲሆን ጥሪም አቅርበዋል።  
በዚህም መሰረት፦
 
1. ከዛሬ ከሰዓት ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ የሚደርሱ እና ለለይቶ መከታተያ በተዘጋጁት ሆቴሎች ለመቆየት አቅም የሌላቸው መንገደኞች ወደ አዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ተዛውረው ከውጪ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ መንገደኞች ለ15 ቀናት ተለይተው እንዲቆዩ የወጣውን መመሪያ ተግባራዊ የሚያደርጉ ይሆናል፡፡
 
2. ከዛሬ አንስቶ ለተጨማሪ ሁለት ሳምንታት ከፍተኛ የትምሕርት ተቋማትን ጨምሮ፣ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው የሚቆዩ ይሆናል፡፡
 
3. በገበያ ስፍራዎች እና በሀይማኖት ተቋማት ውስጥ ማኅበራዊ ርቀትን መጠበቅ በጥብቅ ተፈጻሚ ሊደረጉ ያስፈልጋል፡፡ የፌደራል መንግሥት አስከፊ ብሔራዊ አደጋ በሚከሰት ጊዜ ሀይማኖታዊ ስብሰባዎች እንዲቋረጡ የማድረግ ሕገመንግሥታዊ መብት አለው፡፡ ሆኖም፣ በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉትን እርምጃዎች ተግባራዊ ከመደረጋቸው በፊት፣ ዜጎች የማኅበራዊ ርቀት መመሪያን ተግባራዊ እንዲያደርጉ በድጋሚ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
 
4. ሁኔታው ተጨማሪ ድጋፍን የሚጠይቅ ከሆነ ሁሉም ጡረታ የወጡ እንዲሁም በትምሕርት ላይ ያሉ የሕክምና ባለሙያዎች ለብሔራዊ ግዳጅ እንዲዘጋጁ ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡
 
5. የተለያየ መጠን እና ዓይነት ያላቸው መገልገያዎችን የያዙ ከ134 በላይ ተቋማት ለለይቶ መከታተያ፣ ለይቶ ማቆያ እና ሕክምና እንዲሆኑ ተለይተዋል፡፡ ስለዚህ፣ መንግሥት ሁሉም ዜጎች እንደ አልጋዎች፣ ፍራሾች፣ አንሶላዎች፣ የመተንፈሻ ቬንትሌተሮች እና ሌሎች ከሕክምና ጋር ተያያዥነት ያላቸው እና የሌላቸው መገልገያዎችን ለማሰባሰብ በመሥራት ላይ የሚገኘውን የብሔራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ጥረት እንዲደግፉ ጥሪ ያቀርባል፡፡
 
6. የማክሮ-ኢኮኖሚ ንዑስ ኮሚቴው ኢኮኖሚው ዘርፉን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ አማራጮችን ለመቀየስ በልዩ ልዩ ዘርፍ ከተሠማሩት ዐበይት የኢንደስትሪ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይትን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ ይህንኑ ተከትሎም፣ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት የሚከተሉት እርምጃዎች ተፈጻሚ ይሆናሉ፡-
 
የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስፈልጉ የገቢ ዕቃዎች እና ግብአቶች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ይደረጋል፡፡
 
የፋይናንስ ዘርፉን ጤንነት አስጠብቆ የመቀጠል እና ባንኮች በኮቪድ-19 ቫይረስ ለተጎዱ ደንበኞቻቸው ጊዜያዊ የብድር እፎይታ እና ተጨማሪ ብድር ለመስጠት እንዲያስችላቸው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተጨማሪ 15 ቢሊየን ብር ለግል ባንኮች ይሰጣል፡፡
 
የውጪ ምንዛሬ የሚያስፈልጋቸው እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችሉ ዕቃዎችን እና ግብአቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለሚያስገቡ አስመጪዎች ባንኮች ቅድሚያ በመስጠት እንዲያስተናግዱ ይደረጋል፡፡
 
በፋይናንስ አገልግሎት የተነሳ ገጽ ለገጽ መገናኘት እና የብር ንክኪን ለመቀነስ እንዲቻል፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሞባይል አማካኝነት የሚደረግ ክፍያ እና ገንዘብ የማስተላለፍ ጣሪያውን ከፍ ያደርጋል፡፡
 
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለውጭ ገበያ በሚቀርብ አበባ ላይ የጣለው ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ገደብ በጊዜያዊነት እንዲነሳ ተደርጓል፡፡
 
ኩባንያዎች የተሻለ የገንዘብ ፍሰት እንዲኖራቸው ለማስቻል፣ የገቢዎች ሚኒስቴር የተጨማሪ እሴት ታክስ አመላለስ ሂደቱን በተለየ መልኩ እንዲያፋጥን ይደረጋል፡፡
 
የኮቪድ-19ን ወረርሽኝ ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የሸቀጦች እጥረት እና አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ለመቆጣጠር በንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር የጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.