Fana: At a Speed of Life!

ሙሽሮች በሠርግ ዝግጅታቸው በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻቸውን እንዲያስታውሱ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጋብቻቸውን የሚፈጽሙ ሙሽሮች በሠርግ ወጪያቸው የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታና የተቸገሩ ወገኖችን ታሳቢ እንዲያደርጉ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቅርበዋል።

የሃይማኖት አባቶቹ የዘንድሮን የሠርግም ይሁን የበዓላት ወጪ ቀነስ በማድረግ በጦርነቱ የተጎዱትን መርዳት፣ ከቀያቸው የተፈናቀሉትንም ወደ ቀደመ ኑሯቸው መመለስ ይገባል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሃይማኖት አባቶች ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ ክህነት የቅርስ፣ ላይብረሪና ሙዚየም ዋና ኃላፊ ዶክተር መልዓከ ሠላም አባ ቃለጽድቅ በጥር ወር ጋብቻቸውን የሚፈጽሙ ሙሽሮችም ሠርጋቸውን ሲፈጽሙ የተፈናቀሉ ዜጎችን በማሰብ እንዲሆን ጠይቀዋል።

ደስታን ከተቸገሩ ጋር ማሳለፍን የሃይማኖቱ አስተምህሮ ያዛል ያሉት ዶክተር መላዕከ ሠላም ፥ ተጋቢዎች ቢችሉ በቃልኪዳን ብቻ አልያም በፈልጉት አማራጭ በቀላሉ በመፈጸም ወጪያቸውን እንዲለግሱም ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች የዑላማ ምክር ቤት አባልና የሠላምና እርቅ ዘርፍ ኃላፊ ሼህ መሀመድ ሲራጅ ፥ በቅርቡ ሠርጋቸውን ለመደገስ ያቀዱ ጥንዶች ከወጪያቸው ለተጎዱ በማጋራት በዘመናቸው ታሪክ ለመስራትና ለልጆቻቸውም በጎ-ምግባርን ለማስተላለፍ ይህ ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን ቤተክርስቲያን ኅብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻዲቁ አብዶ በበኩላቸው ፥ የህሊና እርካታ ለማግኘትና የፈጣሪንም ትዕዛዝ ለመፈጸም የተፈናቀሉ ዜጎችን ማገዝና መርዳት ላይ ኃላፊነት መውሰድ ይገባል ሲሉ መክረዋል።

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ላዛሪስት ገዳም አስተዳዳሪ አባ አብነት አበበ ፥ ሕዝብ ተቸግሮ ደስታን ለብቻ ማሳለፍ ከባድ ስለሆነ ወገኖችን በመርዳት ማሳለፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

መላው ህዝብ ለመከላከያ ሰራዊቱ እያደረገ ላለው ያልተቋረጠ ድጋፍና ደጀንነት የሃይማኖት አባቶቹ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ፥ ይህንን በጎ ተግባር ማስቀጠል የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.