Fana: At a Speed of Life!

ሚኒስቴሩ ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በ18 ከተሞች ውስጥ ፋይል የማደራጀት ስራ እያከናወነ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 6፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በ18 ከተሞች ውስጥ የከተማ መሬት ፋይል የማደራጀት ስራ እያከናወነ ይገኛል፡፡

ሚኒስቴሩ የከተሞችን ፋይል የማደራጀት ስራ ለመስራት በዓለም አቀፍ ጨረታ ኤ.ኤች.ሲ ከሚባል የዩጋንዳ አማካሪ ድርጅት ጋር ውል በመያዝ ወደ ትግበራ የተገባ ነው፡፡

ስራው በዋናነት ማዕከል የሚያደርገው የተሟላና በኮምፒዩተር የታገዘ የከተሞች የመሬት ይዞታ እና መሰረታዊ የማዘጋጃ ቤት ገቢ የፋይል አያያዝ ስርዓትን የማጎልበት ስራ ነው፡፡

በዚህ ማዕቀፍ በሌሎች የፋይል መልሶ ማደራጀትና የቅድም-ይዞታ ማረጋገጥ ስራዎችን የማገዝ፣ የንብረት መብት ምዝገባ ሂደትን ለማቀላጠፍ እና ለማፋጠን ከመሬት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ስራዎችን በሚፈለገው ጥራትና በወቅቱ ለማከናወን የሚረዳ ስርዓትን የመፍጠር እንዲሁም የማዘጋጃ ቤት ገቢ አስተዳደር ተቋማትን ለመደገፍ እንደ ግብዓት ሆኖ የሚያገለግል ስርዓት ለመፍጠር ይሰራሉ፡፡

አማካሪ ድርጅቱም በሀረሪ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በደቡብ እና በሲዳማ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ ከተሞች እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በ18 ከተሞች ውስጥ 630 ሺህ የሚሆኑ የመሬት ፋይሎችን በብሎክ የማደራጀት ስራን ይሰራል፡፡

አማካሪ ድርጅቱም ለካዳስተር ስራም ዝግጁ እንዲሆኑ የማድረግ ስራን ጨምሮ፤ ፋይሎችን ስካን በማድረግ መረጃውን በኮምፒዩተር በማደራጀት ዳታ ቤዝ ውስጥ በማስገባት ዘመናዊና የተቀላጠፈ አሰራር እንዲኖር ያደርጋል፡፡

ይህም ከዚህ በፊት በመሬት ሃብት አያያዝ ዙሪያ ይስተዋል የነበረውን አግባብ ያልሆነ የመረጃ አያያዝ ለማስቀረት ቁልፍ መሳሪያ እንደሆነ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መስፍን አሰፋ መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.