Fana: At a Speed of Life!

ሚኒስቴሩ 25 ጊጋ ዋት ተጨማሪ ኃይል ለማመንጨት ፎርቲስኪው ከተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር ተወያየ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር 25 ጊጋ ዋት ተጨማሪ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል ውይይት ፎርቲስኪው ከተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር አካሄደ።

ድርጅቱ 15 ጊጋ ዋት ከውኃ እና 10 ጊጋ ዋት ከጂኦ ተርማል ለማመንጨት  10 በቢሊየን ዶላር ኢንቨስት ለማድረግ እንደሚፈልግ አሳውቋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ በሸራተን አዲስ ሆቴል በተደረገው ውይይት የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ይህ ለኢትዮጵያ ትልቅ እድል ነው ሲሉ ገልጸዋል።

አሁን በኢትዮጵያ 45 በመቶ ብቻ የሆነውን የኃይል ተደራሽነት ለማሻሻል መንግሥት በቅርቡ ሪፎርም ማድረጉን የገለጹት ሚኒስትሩ፥ አሁን ላይ አነስተኛ የሆነውን የኃይል ተደራሽነትን ለማሻሻል ንፁህና ታዳሽ ኃይል በማልማት፣ ዘርፉንም ፋይናንስ በማድረግ፣ የግሉን ባለሃብት የማሳተፍ እንዲሁም ጠንካራ ተቋማትን የመገንባት ሥራ እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል።

በተለይም በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2030 ኢትዮጵያ ለዘጎቿ መቶ በመቶ ኃይል ለማቅረብ ያቀደች በመሆኑ ይህ ውይይትና የድርጅቱ ተነሳሽነት ከፍተኛ ጠቄሜታ ያለው ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ኃይል እያቀረበች እንደሆነና 350 ሜጋ ዋት የደረሰው የኃይል ሽያጭ በጥቂት ዓመታት ወደ 700 ለማሳደግ መታቀዱንም ገልጸዋል።

በተለይ በከተሞች አካባቢ እየጨመረ የመጣው የኢንዱስትሪዎች መስፋፋትና የኃይል ፍላጎት መጨመር ለግል ባለሀብቱ ትልቅ ዕድል እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ሚኒስትሩ ንጹህና ታዳሽ ኃይል ማልማት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ምቹ እንደሆነችና ሰፊ አማራጮችም እንዳሏትም አብራርተዋል።

ፎርቲስኪው የተባለው የዓለም አቀፍ ድርጅት ልዑካን በኢትዮጵያ ሥራ ለመጀመር ይህን ውይይት ያደረጉ ሲሆን፥ ድርጅቱ በአውስትራሊያ፣ በጊኒና በሌሎችም ሃገራት ተመሳሳይ ሥራ በመሥራት ውጤታማ እንደነበር ገለጸው፤ በኢትዮጵያ 25 ጊጋ ዋት ሃይል ለማመንጨት ያላቸውን ፍላጎት ለሚኒስትሩ ገልጸውላቸዋል።

የሚሠሩትም የልማት ሥራ በርካታ ሥራ አጥ ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግና በተለይም ሴቶችን ያሳተፈ እንደሚሆን ማስረዳታቸውን ከውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ፎርቲስኪው በማዕድን፣ በማዳበሪያ፣ በኃይል ማመንጨት፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እና በሌሎችም ሥራዎች ላይ የተሰማራ ዓለም አቀፍ የግል ንግድ ድርጅት ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.