Fana: At a Speed of Life!

ምርት ገበያው በስድስት ወራት ውስጥ የ17 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ምርቶችን አገበያየ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 22 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በበጀት አመቱ ስድስት ወራት 338 ሺህ 253 ሜትሪክ ቶን ምርቶችን በ17 ነጥብ 52 ቢሊየን ብር አገበያየ።

ምርት ገበያው ለጣቢያችን በላከው መግለጫ በስድስት ወሩ ያካሄደው ግብይት ከእቅዱ 5 በመቶ፣ ካለፈው በጀት ዓመት ደግሞ በ28 በመቶ ብልጫ እንዳለው አስታውቋል።

ከዚህ ውስጥ ቡና 45 በመቶ፣ ሰሊጥ 31 በመቶ፣ አኩሪ አተር 10 በመቶ፣ አረንጓዴ ማሾ 8 በመቶ፣ ነጭ ቦሎቄ 5 በመቶ ድርሻ እንዳላቸውም ነው ምርት ገበያው ያስታወቀው።

የሀዋሳ ኤሌክትሮኒክ የግብይት ማዕከል 45 ሚሊየን ብር ግምት ያለው ቡና እንዲሁም በሁመራ ኤሌክትሮኒክ የግብይት ማዕከል ደግሞ 124 ሚሊየን ብር ግምት ያለው ሰሊጥ ተገበያይቷልም ነው ያለው።

የነቀምት የኤሌክትሮኒክ የግብይት ማዕከልም ከጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የሙከራ ስራ የሚጀምር ሲሆን የጎንደርና የአዳማ የኤሌክትሮኒክ የግብይት ማዕከል የፊዚካል ግንባታ መጠናቀቁንም ገልጿል።

ከዚህ ባለፈም በአዲስ አበባ (ሳሪስ) ቅርንጫፍ ተገበያዮች ናሙና አይተው ሊመርጡና ሊገበያዩ የሚችሉበት የምርት ናሙና ማሳያ ሥፍራም በሙከራ ደረጃ ተዘጋጅቶ ሥራ ጀምሯል ብሏል።

እንዲሁም የግብይት መረጃ ለማሰራጨት የሚረዱ 66 የገበያ መረጃ ማሰራጫ ኪዮስኮች በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ ቅርንጫፎች ሥራ መጀመራቸውንም ጠቅሷል።

በተጨማሪም ምርት ገበያው ለመጋዘን ኪራይ የሚያወጣውን ወጪ ለመቀነስ በተለያዩ ስፍራዎች መጋዘኖችን እየገነባ ይገኛል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.