Fana: At a Speed of Life!

ምርት ገበያው በወሩ 5 ነጥብ 12 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው ከ101 ሺህ በላይ ቶን ምርቶችን አገበያየ

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በታህሳስ ወር 5 ነጥብ 12 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው 101ሺህ 948 ቶን ምርቶችን ማገበያቱን ገለፀ።

ምርት ገበያው ሰሊጥ፣ ቡና፣ ነጭ እና ቀይ ቦሎቄን ጨምሮ ነው የተጠቀሰውን ቶን ማገበያት የቻለው።

በዚህም በወሩ ለግብይት የቀረበው 52 ሺህ 598 ቶን ሰሊጥ በ2 ነጥብ 24 ቢሊየን ብር ሲያገበያይ የሁመራ ጎንደር ሰሊጥ 90 በመቶ የግብይት መጠንና ዋጋ በማስመዝገብ ከፍተኛ ድርሻ ይዟል።

ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የግብይት መጠኑ በ34 በመቶ እንዲሁም የግብይት ዋጋው በ26 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፥ አማካይ ዋጋው ግን በአምስት በመቶ ቀንሷል።

በተመሳሳይ 8 ሺህ 565 ቶን ነጭ ቦሎቄ በ176 ሚሊየን ብር ሲገበያይ 8 ሺህ 100 ቶን አረንጓዴ ማሾ በ270 ሚሊየን ብር ተገበያይተዋል።

ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀርም በመጠን የ171 በመቶ በዋጋ የ183 በመቶ ጭማሪን ያሳየ ሲሆን፥ አጠቃላይ ዋጋውም በሶስት በመቶ አድጓል።

የአረንጓዴ ማሾ ግብይትም ካለፈው ወር ጋር ሲተያይ በመጠን 49 በመቶና በዋጋ 63 በመቶ፤ በአማካይ የግብይት ዋጋውም በዘጠኝ በመቶ ጨምሯል።

በተጠቀሰው ወር ለግብይት የቀረበው 30 ሺህ 416 ቶን ቡና በ2 ነጥብ 47 ቢሊየን ብር የተሸጠ ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ቡና 59 በመቶ የግብይት መጠንና 58 በመቶ የግብይት ዋጋ አስመዝግቧል።

የቡና ግብይት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር የግብይት መጠኑ በ10 በመቶ የግብይት ዋጋው ደግሞ በ31 በመቶ እንዲሁም አማካይ ዋጋው በ24 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

በሌላ በኩል 1 ሺህ 876 ቶን አኩሪ አተር ለግብይት ቀርቦ በ22 ሚሊየን ብር ተገበያይቷል። ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀርም በመጠን 73 በመቶ በዋጋ 36 በመቶ ጨምሯል።

በአጠቃላይም በግብይቱ የጥራጥሬና የቅባት እህል ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር መሻሻልን አሳይቷል ነው የተባለው።

በተጨማሪም ምርት ገበያው የበቆሎ ምርትን ከ11 ዓመት በኋላ ዳግም ለማገበያየት የግብይት ኮንትራቱን ለማሻሻል እና የመጋዘን ብድር አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን የገለፀ ሲሆን፥ የመጀመሪያው አቅርቦትም በቡሬ ቅርንጫፍ መከናወኑን ነው ምርት ገበያው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ ያመለከተው።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.