Fana: At a Speed of Life!

ምንም ዓይነት የማሽከርከር ልምድ ያልነበረው ግለሰብ የአስር ሰዎችን ህይዎት ለህልፈት ዳረገ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)ከተወሰነለት ፍጥነት በላይ ሲያሸከረክር በሰዉ ህይወትና አካል ላይ ጉዳት ያደረሰዉ አሽከርካሪ በ8ዓመት ፅኑ እስራትና በገንዘብ መቀጣቱን የጉራጌ ዞን ዓቃቤ ህግ መምሪያ አስታወቀ።

ተከሳሽ ሾፌር አቶ አዳነ አበባው ዳምጤ የሠውን ህይወት የመጠበቅ ሙያዊ ግዴታ ነበረበት።

በቀን 13/ 3/2013 ዓመተ ምህረት ከቀኑ 9 ሰዓት በጉራጌ ዞን ቀቤና ወረዳ በፈረጀቴ ቀበሌ ልዩ ስሙ ሙዞ አካባቢ ኮድ 3 13 6 55 ኦሮ የሕዝብ ማመላለሻ ከአዲስ አበባ ወደ ወልቂጤ ጭኖ በማሽከርከር ላይ ሳለም በሰዉና በንብረት ላይ አደጋ አደረሰ።

ግለሰቡ በቸልተኝነትና በጥንቃቄ ጉድለት ከተፈቀደለት የፍጥነት ወሰን በላይ በማሽከርከር፣ በማይፈቀድለት መታጠፊያ ላይ ደርቦ ከፊት ለፊት ከጅማ ወደ አዲስ አበባ እየተጓዘ ከነበረ ኮድ 3 99 5 67 እና ከተሳቢ ኮድ 33 0205 ኢት ነዳጅ ከጫነ ቦቴ ጋር ከራሱ መስመር ወጥቶ ተጋጭቶ በመገልበጡ ከውስጡ ከነበሩ ተሳፋሪዎች አስር ሰዎች በከፍተኛ ጉዳት ወዲያው ህይወታቸው አለፈ።

ከዚህ በተጨማሪም 18 ሰዎች ላይም ከፍተኛ ጉዳት ደርሰባቸው ።

በጉራጌ ዞን አቃቤ ህግ መምሪያ የልዩ ልዩ ወንጀሎች ዋና ዓቃቤ አቶ ተስፋዬ ሳህሌ እንደገለጹት÷ በዕለቱ በዋለው ችሎት በሰው ህይወትና ከፍተኛ የአካል ጉዳት ያደረሱ የትራፊክ አደጋዎች ክሶች ላይ የቅጣት ውሳኔ መሠጠቱን ገልፀዋል።

በዞኑ በአሽከርካሪዎች ስነ ምግባር ጉድለት፣በቸልተኝነት፣ ከተወሰነላቸው ፍጥነት በላይ በማሽከርከር እና መሠል ምክንያቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ አደጋ አሳሳቢ ነው ብለዋል።

የመኪና ባለንብረቶች ሾፌሮችን ሲቀጥሩ ከመንጃ ፍቃድ ባሻገር የሾፌሩ ልምድ ፣ ግብረ ገብ የሆነ ስነ ምግባር መኖሩንና ከተለያዩ ደባል ሱሶች ነፃ መሆኑን ሳያረጋግጡ እንዲያሽከረክሩ ባለ መፍቀድ ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

አቶ ተስፋዬ ይህን ያሉት የአስር ሰዎች ህይወት እንዲቀጠፍና በ18 ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ያደረሰው አሽከርካሪ ከመንጃ ፈቃድ ውጪ ከዚያ ቀን ውጪ ምንም ዓይነት የማሽከረከር ልምድ እንዳልነበረውና የስነ ምግባር ችግር ጭምር እንደነበረበትም በማስረጃ ተረጋግጧል።

አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የትራፊክ አደጋን ለመከላከል የመንገድ ትራፊክ ፖሊስ፣ የመንግስት የመንገድ ደህንነት ተቆጣጣሪ ባለሞያዎች፣ መላው ህብረተሠብና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መልኩ በጋራ ሊሰሩ ይገባል ማለታቸውን ከዞኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.