Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ እንዲካሄድና የኮቪድ 19 ወረሽኝን መከላከልን መሰረት ያደረገ የምርጫ ዝግጅት እንዲጀመር ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በተያዘው ዓመት እንዲካሄድ እና የኮቪድ 19 ወረሽኝን መከላከልን መሰረት ያደረገ የምርጫ ዝግጅት እንዲጀመር ውሳኔ አሳለፈ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ አስቸኳይ ስብሰባውን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በዛሬው እለት አካሂዷል።

በአስቸኳይ ስብሰባውም  የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉደዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የጤና ሚኒስቴር ሀገራዊ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምላሽ ቀጣይ እርምጃዎችን በተመለከተ ባቀረበው ሪፖርትና ምክረ ሀሳብ ላይ ያቀረቡትን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ በዝርዝር ተመልክቶ በአንድ ተቃውሞ፣ በስምንት ተአዕቅቦ፤ በአብላጫ ድምፅ አጽድቆታል።

በዚህም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን መከላከልን መሰረት በማድረግ ክልከላ የተጣለባቸው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲፈቀዱ እና ትምህርት ቤቶችም እንዲከፈቱ ሲል ነው ውሳኔ ያሳለፈው።

እንዲሁም 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በተያዘው ዓመት እንዲካሄድ የኮቪድ 19 ወረሽኝን መከላከልን መሰረት ያደረገ የምርጫ ዝግጅት አንዲጀመር ወስኗል።

በውሳኔውም በየደረጃው የሚገኙ የሚመለከታቸው አካላት ማስፈጸሚያ መመሪያ እና አሰራሮችን በመዘርጋት፤ ጥብቅ ክትትል እና ቁጥጥር እንዲደረግ ወስኗል።

በተያያዘ ምክር ቤቱ በእስካሁኑ ቆይታውም በጠቅለይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የቀረቡትን የሚኒስትሮች ሹመት እንዲሁም የዳኞችን ተመልክቷል።

በዚህም መሰረት፦

  1. ዶክተር ቀነዓ ያደታ የኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር
  2. ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ
  3. ዶክተር ሳሙኤል ሁርቃቶ የኢፌዴሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር
  4. ኢንጅነር ታከለ ኡማ የኢፌደሪ ማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው የቀረቡለት ሲሆን፥ ምክር ቤቱ የቀረበውን ሹመት በ5 ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ የ40 የከፍተኛ ፍርድ ቤት  እጩ ዳኞችን ሹመት በ5 ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ እንዲሁም የ50 የመጀመሪያ ፍርድ ቤት እጩ ዳኞችን ሹማት ደግሞ በ3 ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።

እጩ ዳኞቹም በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ አማካኝነት በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው ቃለመሃላ ፈጽመዋል፡፡

 

በሀይለኢየሱስ ስዩም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.