Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከቀረቡት ዕጩ ኮሚሽነሮች መካከል 42ቱን መለየቱን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክት ቤት ለሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነርነት ከቀረቡት ዕጩዎች መካከል 42ቱን መለየቱን የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ አስታወቁ፡፡

አፈ-ጉባኤው በጉዳዩ ላይ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፥ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ ቁጥር 1265/14 መቋቋሙንና በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ዕጩ ኮሚሽነሮች እንዲጠቆሙ በሁሉም የሀገሪቱ የመገናኛ ብዙሀን መተላለፉን አስታውሰዋል።

የጥቆማ ማቅረቢያ ጊዜው እንዲራዘም የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ማህበራት በአካልና በጽሁፍ በጠየቁት መሰረት የሁሉም አካላት ተሳትፎ እንዲረጋገጥ ምክር ቤቱ ለአንድ ሳምንታት ማራዘሙን እና ባለፉት ሳምንታትም ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የምክር ቤቱ ፅህፈት ቤት የዕጩ ኮሚሽነሮችን ጥቆማ ሲቀበል መቆቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ከመላው የሀገሪቱ ክፍሎች 632 የእጩ ኮሚሽነሮች ጥቆማ መቅረባቸውንና አብዛኛዎቹ ስራውን ለመስራት የሚያስችል ልምድና ዕውቀት ያላቸው መሆኑን መገንዘብ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

አዋጁ ለአፈ-ጉባኤውና ለአፈ-ጉባኤው ጽ/ቤት በሰጠው ስልጣን እንዲሁም በአዋጁ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ከቀረቡት 632 ዕጩዎች መካከል 42ቱ መለየታቸውን ተናግረዋል፡፡

አክለውም በቀረቡት 42 ዕጩ ኮሚሽነሮች ላይ ከአማካሪዎች ጋር ምክክር እየተደረገ መሆኑን ነው አቶ ታገሰ የገለፁት።

በቀጣይ ሳምንትም የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች፣ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመራሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አመራር አካላት በሚገኙበት በዕጩዎች የትምህርት ዝግጅትና የስራ ልምድ ላይ ምክክር ተደርጎ ግብአት የሚሰበሰብ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር በምክር ቤቱ ድረ-ገጽና በማህበራዊ ሚዲያ የእጩዎችን ማንነት በመግለጽ በቂ ግብአት ከተሰበሰበ በኋላ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢን ጨምሮ 11ዱ ዕጩ ኮሚሽነሮች ለምክር ቤቱ ቀርበው ከፀደቁና ዕጩዎች ከተሰየሙ በኋላ ወደ ስራ እንደሚገባም ገልጸዋል።

በመጨረሻም አፈ-ጉባኤው ቀጣይ በሚደረገው ሀገራዊ የምክክር መድረክ ከህዝብ የሚነሱ የተለያዩ ሀገራዊ ሀሳቦች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመው፥ ሀገሪቱ ትልቅ ታሪክ፣ ህዝብ፣ ስነ-ልቦና እና ሀብት ያላት በመሆኑ ሁሉም አካል የሰከነ ውይይት በማድረግ እና መግባባት ላይ በመድረስ የሀገሪቱን የብልፅግና ጉዞ ማረጋገጥ እንደሚገባም ማሳሰባቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.