Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ ምርጫን በተመለከተ የመፍትሄ ሀሳብ እንዲያቀርብ ለህግ፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መራ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው እለት አካሂዷል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የመሰብሰቢያ አደራሽ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባውም የተለያዩ ውሳኔዎችን መርምሮ አጽድቋል።

ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጠቅላላ ምርጫን በተመለከተ ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብን ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርትኳን ሚደቅሳ የጠቅላላ ምርጫን በተመለከተ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ አቅርበዋል።

የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርትኳን ሚደቅሳ ባቀረቡት የውሳኔ ሀሳብም በቦርዱ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ የመራጮች ምዝገባ የሚጀምረው ከሚያዚያ 14 ቀን 2012 ዓ.ም ቢሆንም፤ በሀገሪቱ ውስጥ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሣቢያ በርካታ ህዝብዊ እንቅሰቃሴዎች የተገደቡ በመሆኑ የምርጫው ጊዜው በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ማካሄድ እንደማይቻል ገልጸዋል።

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፥ የምርጫ ቦርድ ከዚህ በፊት ምርጫውን ለማካሄድ የሚችልበትን የጊዜ ሰሌዳ በግልጽ ለህብረተሰበሱ ማስታወቁን አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ ወረርሽኙ በአለምና በአገራችን በመከሰቱ መንግስት ቅድሚያ ለሕዝብና ለሀገር በሚል በርካታ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል፤ ሲለሆነም ቦርዱም ከዚህ ጊዜ ምርጫ ማካሄድ እንደማይቻል መግለጹን ተገቢነው ብለዋል።

ቦርዱ የምርጫ ጊዜው እንዲራዘም ምክረ ሀሳብ ማቅረቡ ተገቢ ቢሆንም በሀገሪቱ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስን ወረርሽኝ ነው ለማለት ይቻላል ወይ? የሚል ጥያቄ አዘል አስተያየት አቅርበዋል።

በርካታ ቁጥር ያላቸው የምክር ቤት አባላት በሽታው ወረርሽኝ እንደሆነና መንግስት ወረርሽን መሆኑን አምኖ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከማወጁ በላይ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ መዝጋቱንና ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎችን መገደቡን ጠቁመው ቦርዱ ያቀረበውን ውሳኔ ተቀብሎ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መምራቱን አግባብ መሆኑን አብራርተዋል።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፥ ቦርዱ ተጠሪነቱ ለምክር ቤቱ መሆኑንና የመጨረሻ ውሳኔም የምክር ቤቱ መሆኑን ጠቁመው የቀረበውን የመፍትሄ ሀሳብ ለድምጽ አቅርበዋል።

በዚህም መሰዘረት ምክር ቤቱ ውሳነውንም ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጠቅላላ ምርጫን በተመለከተ ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በአንድ ተቋሞና በ18 ድምጸ ታዕቅቦ በአብላጫ ድምፅ አጽድቆታል።

በመቀጠልም ምክር ቤቱ ምርጫን በተመለከተ የመፍትሄ ሀሳብ እንዲያቀርብ ለህግ፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በ3 ተቃውሞ፣ በ7 ድምፀ ተአቅቦና በአብላጫ ድምጽ መርቷል።

ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በሳዑዲ የልማት ፈንድ መካከል ለሁለተኛው አገር አቀፍ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ሳኒቴሽንና ሃይጂን ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነትን በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።

ኢትዮጵያ ከኮሪያ ኤክስፖርት – ኢምፖርት ባንክ ጋር ለአዳማ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የልህቀት ማዕከል መመስረቻ፤ ከሳዑዲ የልማት ፈንድ ለደብረ ማርቆስ – ሞጣ የመንገድ ሥራ ማሻሻያና ማሳደጊያ ፕሮጀክት፤ ከዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ለቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነቶችን ተመልክቶ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽንን ለመደንገግ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለሰው ሃብት ልማትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እየታ በሙሉ ድምጽ መርቶታል።

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.