Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ በሀገሪቱ የሀሳብ ልዩነትን መነሻ አድርገው የሚከሰቱ ግጭቶች በሰለጠነ መንገድ ሊፈቱ ይገባል አለ

አዲስ አበባ፣ጥር 19፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሀገሪቱ የሀሳብ ልዩነትን መነሻ አድርገው የሚከሰቱ ግጭቶችና የጦርነት አዙሪት በሰለጠነ መንገድ ሊፈቱ እንደሚገባ አስገነዘበ።
የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለሁለት ቀናት ያካሂደው ውይይት ዛሬ ተጠናቋል።
ለምክር ቤቱ አባላት በቀረበው የውይይት ሰነድ መነሻነት፥ ጦርነቱ ያለበትን ደረጃ፣ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ፣ የፀጥታ እና አጠቃላይ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ ላይ በዝርዝር ተወያይተዋል፡፡
የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ፥ በኢትዮጵያ መግባባት ላይ ያልተደረሰባቸውና የሀገሪቱን ህልውና የሚፈታተኑ የተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር በማድረግ ለመጪው ትውልድ ሰላማዊ ሀገር ለማስረከብ ሁሉም ዜጋ በሀገራዊ ጉዳይ ላይ የመወሰን መብቱን በመጠቀም ሃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው፥ በሀገሪቱ ያለውን የፖለቲካ ባህል መቀየር እንደሚገባ ገልፀው፥ የሀሳብ ልዩነትን መነሻ አድርገው የሚከሰቱ ግጭቶችና ጦርነቶች በሰለጠነ መንገድ ሊፈቱ ይገባል ብለዋል፡፡
ኀብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ለዘመናት ከዘለቀው የፖለቲካ ቀውስ አዙሪት በመውጣት እስካሁን በጦርነቱ የተጎዳውን የሀገር ኢኮኖሚ መልሶ ለመገንባት በየደረጃው ያለ የህብረተሰብ ክፍል ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተቃጣውን አደጋ መላው ህዝብ ያለምንም ልዩነት በአንድነት በከፈለው መስዋትነት የጠላትን ፍላጐት መቀልበስ እንዳስቻለ ሁሉ፣ በቀጣይም ከጦርነቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን መቋጨት ፣ የውስጥ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ አንድነታችንን ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡
በጦርነቱ የወደሙ ተቋማትንና መሰረተ ልማቶችን እንዲሁም አካባቢዎችን መልሶ ማቋቋምና የመከላከያ ሰራዊቱን ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሠራ ነው አቶ ተስፋዬ የገለጹት፡፡
የኢፌድሪ የህዝብ ተወካዮቸ ምክር ቤት በሀገሪቱ የመጨረሻው የስልጣን አካል እንደመሆኑ መጠን፥ ሀገሪቱ ከገባችበት ዘርፈ ብዙ ችግር ለማሻገር የምክር ቤት አባላት የማይተካ ሚና እንዳላቸው አውቀው፥ ኃላፊነታቸውን በብቃት ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ኢትዮጵያ በነፃነት ታሪኳ እና የዓባይ ወንዝ መነሻ በመሆኗ በዓለም ኃያላን መንግስታት በልዩ ትኩረት ውስጥ እድትገባ እንዳደረጋት ጠቅሰው፥ ከውስጥ ባንዳዎች ጋር በመተባበር ሀገር ለማፍረስ የተነሱበትን መንገድ እና መዳረሻ ህልማቸውን በተባበረ ክንድ ማክሸፍ መቻሉንም አንስተዋል፡፡
ምክትል አፈጉባኤ ወ/ሮ ሎሚ በዶ በበኩላቸው፥ በጦርነቱ በተከሰተው ቀውስ የተጎዱ አካባቢዎችና የህብረተሰብ ክፍሎች ስነልቦና በመገንባት እንዲሁም መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ርብርብ ምክር ቤቱ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡት የምክር ቤት አባላት ስለተወከሉበት ህዝብና አካባቢ በቂ መረጃ በመያዝ ከማህበራዊ ድህረ-ገፅና ከአንዳንድ የሚዲያ አውታሮች የተዛባ መረጃ ራሳቸውንና ዜጎችን እንዲጠብቁ አሳስበዋል፡፡
በስልጠናው የተሳተፉ የምክር ቤት አባላትም በጦርነቱ የተገኘውን ድል በማስቀጠል፥ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያገግም እና ሰላምና ፀጥታ እንዲረጋገጥ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ማረጋገጣቸውንም ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.