Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ የ2012 በጀት ዓመት ተጨማሪ በጀትን አፀደቀ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 21 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌደራል መንግስት የ2012 በጀት ዓመት የተጨማሪ በጀት ላይ ተወያይቶ አፀደቀ።

በዚህ መሰረት የፌደራል መንግስት የ2012 በጀት ዓመት የተጨማሪ በጀት ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ሰፊ ውይይት በማድረግ አዋጅ ቁጥር 1203/2012 ሆኖ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

የኮሮና ወረርሽኝን የኢኮኖሚ ጫናን ለመቋቋም ከውጭ ሀገራት በሚገኝ 28 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር እና ከሀገር ውስጥ ምንጮች በሚገኝ 20 ቢሊየን ብር ለመቋቋም መታቀዱን የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት መንግስት ጥንቃቄ የተሞላበት የብድር ሂደት ይከተላል ማለታቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው የካቲት 9 ቀን 2012 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው ለ2012 በጀት ተጨማሪ 27 ነጥብ 89 ቢሊየን ብር ሆኖ እንዲፀድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መምራቱ ይታወሳል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ የሰው ሀብትና ቴከኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽንን ለመደንገግ የቀረበን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አዋጁን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

ከዚህ ባለፈም የጂኦተርማል ሀብት ልማት አዋጅን ለማሻሸል የቀረበ አዋጅን በሙሉ ድምጽ አፅድቆታል።

እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ከሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ እና የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስልን ህጋዊ ሰውነት ለመስጠት የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ለህግ፣ ፍትህ እና ዴሞኪራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአብላጫ ድምጽ ተመርቷል።

በተጨማሪም የልዩ የመንግስት ዕዳ ሰነድ ረቂቅ አዋጅ የተመለከተ አዋጅን በአብላጫ ድምጽ ለገቢ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 38/2012 ሆኖ መርቶታል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.