Fana: At a Speed of Life!

ምክትል ጠ/ሚ አቶ ደመቀ መኮንን በመኖሪያ ቤታቸው አካባቢ ለሚገኙ ወገኖች ማዕድ አጋሩ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 28 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአስቸጋሪ ወቅት በየመኖሪያ አካባቢ ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን በቅርበት መደገፍ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አስገንዝበዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው አካባቢ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የምግብ እና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ አበርክተዋል።

በወረዳው ፅህፈት ቤት ቅጥር ግቢ በግላቸው ድጋፍ ባበረከቱበት ወቅት፥ በአስቸጋሪ ወቅት በየመኖሪያ አካባቢ ድጋፍ ለሚገባቸው ወገኖች በቅርበት መድረስ ይገባል ብለዋል።

ኮቪድ19 ወረርሽኝን ተከትሎ በገጠሙ ህብረ ብዙ ችግሮች በየመኖሪያ አካባቢው ለሚገኙ አቅመ ደካሞች እና የከፋ የኑሮ ጫና ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን አቅም በፈቀደ መጠን በመደገፍ ችግሩን በጋራ መሻገር እንደሚገባ አስረድተዋል።

ማዕድ የመጋራት ሃገራዊ ጥሪ በተግባር ምላሽ ለመስጠት በየመኖሪያ አካባቢ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች በቅርበት መድረስ መልካም ልምምድ መሆኑንም አንስተዋል።

በዚህ ረገድ በንፁህ ወገናዊ ስሜት በየመኖሪያ አካባቢ ድጋፍ ላበረከቱ ባለሃብቶች ምስጋና በማቅረብ ችግሩ እስከሚያልፍ ድረስ ድጋፋቸውን አቅም በፈቀደ መጠን እንዲያጠናክሩም ጥሪ አቅርበዋል።

የኮቪድ19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያግዙ መሰረታዊ የጥንቃቄ መመሪያዎችን ባለመሰልቸት ተግባራዊ እንዲያደርጉ መናገራቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በመጨረሻም ድጋፍ የተደረገላቸው ወገኖች እና የክፍለ ከተማው ከፍተኛ አመራሮች ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በግል ተነሳሽነት ላበረከቱት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.