Fana: At a Speed of Life!

ምክትል ጠ/ሚ አቶ ደመቀ መኮንን ከፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 17፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ተወያዩ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በአውሮፓ ሃገራት የዲፕሎማሲ ተልዕኮ ጉዟቸው ዛሬ በፈረንሳይ ቀጥሏል።

አቶ ደመቀ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተላከውን መልዕክት ለፕሬዚዳንት ማክሮን አድርሰዋል።

በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ በሚፈለገው ጥራት እና ፍጥነት ለማስቀጠል ከሁለት ዓመታት በላይ መንግሥት አስፈላጊውን ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አስረድተዋል።

ሆኖም የወንበዴው የህወሓት ቡድን በህዝቡ እና በመንግሥት ላይ ተደጋጋሚ ጥፋቶችን ሲፈፅም እንደነበር አስታውሰዋል።

በመንግሥት በኩል ችግሩን በሰላም እና በውይይት ለመፍታት ተደጋጋሚ ጥረቶች ቢደረጉም በአንፃሩ የወንበዴው ቡድን እኩይ ድርጊቶችን መፈፀሙን አጠናክሮ እንደገፋበት ተናግረዋል።

በሂደት አስገዳጅ እና አሳዛኝ ድርጊቶች መፈጠራቸውን ተከትሎ መንግስት ህግ የማስከበር እርምጃ እየወሰደ የመጨረሻው ዘመቻ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ገልፀዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ መንግሥት የውስጥ ጉዳዩን በራሱ ለመፍታት የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን በመጠቆም ህግ በማስከበር እርምጃ ሂደት ለንፁሃን ዜጎች ደህንነት ተገቢውን ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አመላክተዋል።

በዘመቻው የአስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ መንግሥት የጀመረው ጥረት የሚበረታታ በመሆኑ በቀጣይ ለተቀናጀ ሰብዓዊ እርዳታ አስቻይ መደላድሎች እንዲጠናከሩም ጠይቀዋል።

በመጨረሻም የኢትዮ ፈረንሳይ ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች ከደረሱበት የትብብር ምዕራፍ በተሻለ ደረጃ ለማጠናከር መንግስታቸው ዝግጁ መሆኑን ፕሬዚዳንት ማክሮን ማረጋገጣቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.