Fana: At a Speed of Life!

ም/ከ ወ/ሮ አዳነች የኢሬቻ በዓል በሆራ ፊንፊኔ በሰላም እንዲከበር ያስቻሉ አካላትን አመሰገኑ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ በሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል በሰላም ተከብሮ መጠናቀቁን የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለፁ፡፡
ምክትል ከንቲባዋ ከበዓሉ ማብቃት በኋላ በሰጡት መግለጫ፥ አሬቻ በሆራ ፊንፊኔ በድምቀት እና በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ያስቻሉ አባገዳዎች፣ የመዲናይቱ ነዋሪዎች፣ የበዓሉ ተሳታፊዎች እና የፀጥታ አካላትን አመስግነዋል፡፡
በዓሉ በስርዓት እንዳይከበር ለማድረግ የጥፋት ሀይሎች በጀት መድበውና ሀይል አስተባብረው ሲሰሩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ነገር ግን መላው በከተማዋ ነዋሪዎች፣ በበዓሉ ተሳታፊዎች እና በፀጥታ ሀይሎች ትብብር እና በተቀናጀ ስራ ሊከሽፍ ችሏል ነው ያሉት፡፡
በዚህም በሀገር ውስጥም በውጭም የምትገኙ ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል ወይዘሮ አዳነች፡፡
በዓሉ በሰላም ተጠናቀቀ ማለት የጥፋት ሀይሎች አሁንም አርፈው ይቀመጣሉ ማለት አይደለም ያሉት ወይዘሮ አዳነች፥ ለዚህም ደግሞ ህዝቡ ተቀናጅቶ ከፀጥታ ሀይሎች ጋር በመስራት ለቀጣይ ሰላሙ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
ለህዝብ፣ ለእሴትና ለባህል ክብር በሌላቸው ሀይሎች የሀገሪቱ ብልፅግና ጉዞ ሊገታ እንደማይችልም ነው ያረጋገጡት፡፡
ነገም ኢሬቻ በሆራ አርሰዴ ሲከበር በተመሳሳይ በሰላም እንዲጠናቀቅ ማድረግ የሁሉም ድርሻ እንዲሆን አሳስበዋል።

 

በፍሬህይወት ሰፊው
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.