Fana: At a Speed of Life!

በሦስት የእግር ኳስ ዳኞች ላይ የቅጣት ውሳኔ ተላፈ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በወላይታ ዲቻ እና በኢትዮጵያ ቡና የእግር ኳስ ቡድኖች ክስ የተመሰረተባቸው ሦስት የእግር ኳስ ዳኞች ላይ የቅጣት ውሳኔ ተላለፈ፡፡

በኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ የ24ኛ ሣምንት ጨዋታ የኢትዮጵያ ቡና ከሀድያ ሆሳዕና ያደረጉትን ጨዋታ በዋና ዳኝነት የመሩት ፌደራል ዳኛ ሚካኤል ጣዕመ በተጫዋቾች ላይ አላስፈላጊ ቃላትን ስለመጠቀማቸው የኢትዮጵያ ቡና ክስ ማቅረቡን ተከትሎ÷ ጉዳዩን የተመለከተው የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ዳኛው ጥፋተኛ ሆነው ስላገኛቸው ከፕሪሚየር ሊጉ አሰናብቷቸዋል፡፡

በሌላ በኩል ወላይታ ዲቻ እና ሲዳማ ቡና ባደረጉት ጨዋታ ወላይታ ዲቻ ያልተገባ የፍፁም ቅጣት ምት እንደተሰጠበት እና ያገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት የሲዳማ ቡናው ግብ ጠባቂ መስመሩን ለቆ እንዳዳነበት በመግለፅ የዕለቱን ዳኞች ተጠያቂ አድርጓል፡፡

ክሱን የተመለከተው የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴም÷ ጨዋታውን መርተው የነበሩት ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ለሚ ንጉሴ እና ረዳት ዳኛ አብዱ ይጥና የዚህን ዓመት ቀጣይ ጨዋታዎች እንዳይመሩ በሚል ከውድድሩ ማሰናበቱን ሶከር ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.