Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያና ቱርክ በሶሪያ ጉዳይ ተፋጠዋል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሩሲያ እና ቱርክ በሶሪያ ጉዳይ ላይ ያላቸው ልዩነት እየሰፋ ነው።

የተለያዩ ሀገራት በሶሪያ ቀውስ የሚያደርጉት ተሳትፎ ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት የሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል።

በሶሪያው የእርስ በርስ ጦርነት በቱርክ የሚደገፉት የሶሪያ አማጽያን የመንግስትን ጦር ሲዋጉ፥ ሩሲያ በበኩሏ ለበሽር አላሳድ ጦር ድጋፍ ታደርጋለች።

ሃገራቱ ለዘጠኝ ዓመታት በዘለቀው እና 400 ሺህ ሶሪያውያንን ለህልፈት በዳረገው ጦርነት ጎራ ለይተው ድጋፍ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።

በሩሲያ መንግስት የሚደገፈው የሶሪያ ጦር የአማጽያኑን ጠንካራ ይዞታ ለመንጠቅ ከባድ ውጊያ እያደረገ ሲሆን ቱርክ በበኩሏ ከሩሲያና ሶሪያ መንግስት በተቃራኒ በመቆም ለአማጽያኑን ድጋፍ እያደረገች ትገኛለች።

በአካባቢው ምን ተፈጠረ

የቱርክ መከላከያ ሚኒስትር የሶሪያ መንግስት በኢድሊብ ግዛት በፈጸመው የአየር ጥቃት ሁለት ወታደሮቹ እንደሞቱ እና አምስቱ ደግሞ እንደቆሰሉ አስታውቋል።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ቱርክ ሽብርተኞችን እየደገፈች ነው ሲል ኮንኗል።

ቱርክ ለታጣቂዎች የጦር መሳሪያ ድጋፍ እያደረገች ነው የሚለው ሚኒስቴሩ፥ አራት የሶሪያ መንግስት ወታደሮች መቁሰላቸውንም ገልጿል።

በተጨማሪም በአካባቢው በአብዛኛው ህጻናትና ሴቶች የሆኑ 1 ሚሊየን ሰዎች ለስደት መዳረጋቸውን የሩሲያ ጦር አስታውቋል።

ቱርክ በበኩሏ ሩሲያ በኢድሊብ ግዛት የታጣቂዎች ይዞታ ላይ ጥቃት እየፈጸመች የሶሪያ መንግስት ወታደሮች ቦታውን እንዲቆጣጠሩ እገዛ እያደረገች ነው ስትል ትወቅሳለች።

ሃገራቱ በሶሪያ ጉዳይ ያላቸውን ልዩነት ለመፍታት በጠረጴዛ ዙሪያ ተደጋጋሚ ድርድሮችን ቢያደርጉም፥ ወደ ስምምነት ግን መምጣት አልቻሉም።

የአማጽያኑ የመጨረሻ ጠንካራ ይዞታ እንደሆነች በሚነገርላት ኢድሊብ ግዛት፥ ያለው ውጥረት ሩሲያ እና ቱርክ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዳይደርሱ ምክንያት መሆኑም ይነገራል።

ሆኖም የሩሲያ እና ቱርክ ባለስልጣናት ሀገራቱ በአካባቢው ያለውን ውጥረት ለማርገብ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኝ ነው የሚገልፁት።

የሩሲያውን የዜና አገልግሎት ዋቢ ያደረገው የሬውተርስ ዘገባ ደግሞ ሃገራቱ በኢድሊብ ግዛት የተኩስ አቁም በሚደረስበት አግባብ ላይ ሊመክሩ መሆኑን ያመላክታል።

እንደ ዘገባው በግዛቲቱ የተኩስ አቁም መድረስና አሸባሪዎችን ከአካባቢው ማስወጣትን አላማ ያደረገ ድርድር በቀጣይ ይደረጋል።

ምንጭ፦ ሞስኮ ታይምስና ሬውተርስ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.