Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ ለአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት የሚላከውን ጋዝ እንደምታቋርጥ አስጠነቀቀች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት እስትንፋስ የሆነውን ጋዝ ልታቋርጥ እንደምትችል አስጠነቀቀች፡፡
ሊትዋኒያ ወደ ሩሲያ ካሊኒንግራድ ከተማ የሚጓጓዙ አንዳንድ ዕቃዎች ማገዷን ተከትሎ ሩሲያ ለአውሮፓ አባል ሀገሯ የተጠንቀቂ መልዕክት ልካለች፡፡
የቀድሞው የሩሲያ ፕሬዚዳንት ዲሜትሪ ሜድቬዴቭ እንዳሉት፥ ሊትዋኒያ ላስተላለፈችው የእገዳ ውሳኔ “ጠንካራ” የበቀል እርምጃዎች ይጠብቁሻል ብለዋታል፡፡
ሊትዋኒያ የጣለችውን እገዳ ተከትሎ ሩሲያ በአጸፋው ወደ ባልቲክ ሀገራት የሚሄደውን ጋዝ ማቋረጥ እንደአማራጭ ወስዳው ሊሆን እንደሚችል የጠቀሱት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ፣ ጉዳዩ ከባድ ሊሆን እንደሚችል ነው የገለጹት፡፡
ካሊኒንግራድ በሊትዋኒያ እና በፖላንድ መካከል የምትገኝ የሩሲያ አንዷ ከተማ ናት።
ሜድቬዴቭ አክለውም ፥ የአውሮፓ ኅብረት ሩሲያ ላይ እገዳዎችን ጥሏል፤ ይህን ተከትሎም ሊትዋኒያ “ለአሜሪካውያን የዕርዳታ ድርጅቶች ሰግዳለች፤ ለሩሲያም ያላትን ጥላቻ አሳይታለች” ብለዋል።
የመጓጓዣ እገዳው የምዕራቡ ዓለም በሩሲያ ላይ የከፈተው የ”ውክልና ጦርነት” አካል መሆኑን አጉልተው የገለጹት የቀድሞው መሪ ፥ ሀገራቸው የምትወስደው የአጸፋ እርምጃ “በጣም ከባድ” እንደሚሆን ቃሌ ነው ብለዋል፡፡
ሜድቪዴቭ ፥ ብዙዎቹ አጸፋዊ ምላሾች ኢኮኖሚያዊ ባህሪ ያላቸው መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የሩስያ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት ሜድቬዴቭ፥ ሩሲያ ‘ያልተመጣጠነ’ እርምጃዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደምትችል በአጽንኦት መናገራቸውን የዘገበው አር ቲ ነው፡፡
“ሊትዋኒያ እልህ ውስጥ መግባት አያዋጣትም፤ በዚህ ችግር የሚሠቃዩት ደግሞ የሊትዋኒያ ዜጎች ናቸው፤ የኑሮ ደረጃቸው ከአውሮፓውያን መስፈርቶች ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው” ሲሉም ነው ያብራሩት፡፡
የሊትዋኒያው ፕሬዚዳንት ጊታናስ ናውሳዳ ፥ ሀገራቸው እገዳውን እንደምትቀጥል አስታውቀዋል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ዲፕሎማት ጆሴፕ ቦሬል በበኩላቸው ÷ ኅብረቱ በሩሲያ ካሊኒንግራድ ላይ “እገዳ” ለመጣል እንደማይፈልግና የእገዳውን መመሪያ እንደሚገመግም ቀደም ሲል መግለጹን አርቲ አስታውሷል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.