Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራ ትቀጥላለች – ፑቲን

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥል ፕሬዚዳንት ፑቲን አረጋገጡ፡፡

ፑቲን የሰሜን ኮሪያን የነፃነት ቀን አስመልክተው ለሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በላኩት ደብዳቤ እንደገለፁት የሩሲያ እና የሰሜን ኮሪያ ግንኙነት መጠናከር  የሀገራቱን የጋራ ጥቅም ያስጠብቃል፡፡

ኪም ጆንግ ኡን በበኩላቸው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጃፓንን ድል ለማድረግ ሁለቱ ሀገራት የነበራቸው ወታደራዊ ትብብር የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት መነሻ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ይህ የሀገራቱ “ጓዳዊ ወዳጅነት” የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መናገራቸውን የሀገሪቱን ሚዲያ ኬ ሲ ኤን ኤን ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት በአንድ ወቅት የሰሜን ኮሪያ ዋነኛ አጋር የነበረች ሲሆን፥ ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ጨምሮ የባህል ልውውጥ እና የተለያዩ ድጋፎችን ታደርግ እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ በምስራቅ ዩክሬን የሚገኙና በሩሲያ የሚደገፉ የዶኔስክ እና ሎሀንስክ ተገንጣይ ግዛቶችን በይፋ እውቅና ከሰጡ  ሀገራት አንዷናት፡፡

ዩክሬን በበኩሏ የሰሜን ኮሪያን ውሳኔ ተከትሎ ከፒዮንግያንግ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማቋረጧ የሚታወስ ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.