Fana: At a Speed of Life!

ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ለአሸንድዬ፣ ሻደይ እና ሶለል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶክተር) ለአሸንድዬ፣ ሻደይና ሶለል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
 
ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ባህል የአንድ አካባቢ ሕዝቦች የአብሮነታቸው ማሳያና የማንነታቸው መገለጫ ከመሆኑ ባሻገር የለውጥና እድገት እንዲሁም የኪነጥበብና ሥልጣኔ ምልክት መሆኑን አውስተዋል፡፡
 
በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች አሸንድዬ፣ ሻደይና ሶለል በዓል በልዩ ልዩ ባሕላዊ ክዋኔዎች ይከበራሉ፤ በዓላቱ ወጣቶችና ልጃገረዶች አደባባይ ወጥተው፣ በአንድነት ተሰባስበው ባሕልና እሴቶቻቸውን በመግለጽ የሚያሳልፉበትና በመካከላቸው ጠንካራ የባሕል ትስስር የሚፈጥሩበት ነው ብለዋል።
 
በዓላቱ በሕዝቦች መካከል ማህበራዊ ትስስር በመፍጠር አንድነትን እንደሚያጠናክሩ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ በአንድነት ውስጥ መተዋወቅና መከባባርን፤ በመከባባር ውስጥ ደግሞ የጋራ ሰላምና ልማትን ይገነባሉ ነው ያሉት።
 
በዓላቱን ወቅት ጠብቀን ከማክበር ባለፈ በቅርስነት ጠብቀን፣ ለክልላችን ቱሪዝም ልማት እድገት የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ በአግባቡና በተገቢው መንገድ በማስተዋወቅ ልንጠቀምባቸው የሚገቡ እሴቶቻችን ናቸው ብለዋል።
 
ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል የአሸንድዬ፣ ሻደይ እና ሶለል በዓላት ሲከበሩ መረዳዳትና መደጋገፍ በተግባር የሚታይበት እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.