Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስ ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል – የክልሉ ኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ሃይል

አዲስ አበባ ፣ ሐሌ 25 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በከፍተኛ ፍጥነት እያሻቀበ በመምጣቱ ህብረተሰቡ ከአላስፈላጊ መዘናጋት መውጣት እንዳለበት የአማራ ክልል ኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ሃይል አሳሰበ።

የግብረ ሃይሉ አስተባባሪ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ እንዳሉት በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከእለት ወደ እለት በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ነው።

የቫይረሱ ስርጭት በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመረ ቢመጣም ህብረተሰቡ ቫይረሱን ለመከላከል የሚያደርገው ጥረት በተቃራኒው መዘናጋት እንደሚታይበትም ገልፀዋል።

በትናንትናው እለት ብቻ 22 ሰዎች በክልሉ የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የገለጹት አስተባባሪዋ ህብረተሰቡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መመሪያዎችን በጥብቅ ስነ ምግባር ሊተገብር ይገባል ብለዋል።

የክልሉ መንግስት ቫይረሱን ለመከላከል የተለያዩ አደረጃጀቶችን ፈጥሮ ለመከላከል የሚያስችሉ መመሪያዎችን የማስገንዘብ ስራ እየሰራ ቢሆንም ህብረተሰቡ የሚወርዱ መመሪያዎችን እየተገበረ አይደለምም ነው ያሉት።

በዚህም በቫይረሱ የሚያዙም ሆነ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ በመምጣቱ ህዝቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የጤና ተቋማት ተሰሚነታቸውን ተጠቅመው እየተቀዛቀዘ የመጣውን ቫይረሱን የመከላከል ጥንቃቄ ህብረተሰቡን በማስተማር እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።

ከዛሬ ጀምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ የማያደርጉ ተግልጋዮችን ማስተናገድ እንደሌለባቸውም አስታውቀዋል።

በተለይም በባህርዳር ከተማ ማንኛውም ሰው ከቤት ውጭ ለሚያከናውናቸው ተግባራት የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል የማድረግ ግዴታ መጣሉን አስረድተዋል።

የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል በማያደርጉ ሰዎች ላይ ፖሊስ ግዴታውን የማስከበር እርምጃ እንዲወስድ ትዕዛዝ እንደተላለፈ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.