Fana: At a Speed of Life!

ሰራዊቱ መቐለን እና የወንጀለኛው ጁንታ ቡድን አባላትን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ስትራቴጂክ ቦታዎችን ያዘ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 18 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሃገር መከላከያ ሰራዊት መቐለን እና የወንጀለኛው ጁንታ ቡድን አባላትን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ስትራቴጂክ ቦታዎች መያዙን አስታወቀ።

የትግራይ ህዝብ ከመጀመሪያው ዕለት አንስቶ ለመከላከያ ሰራዊት ወገንተኝነቱን አሳይቷል።

የሃገር መከላከያ ሰራዊት ሀውዜን፣ አል ነጃሺ፣ አዲቀየህ፣ ማይመሳኖን እና ውቅሮን ከጁንታው ታጣቂ ሃይል ሙሉ በሙሉ ነፃ አድርጓል።

የህወሓት ጁንታ በሰላም እጁን እንዲሰጥ መንግስት የሰጠውን የ72 ሰዓታት ጊዜ ሊጠቀም ባለመቻሉ ከትናንት ጀምሮ የህግ ማስከበር ስራው ቀጥሏል።

በመከላከያ ሰራዊት ህብረት ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ሀሰን ኢብራሂም በሰጡት መግለጫ የህግ ማስከበር ሂደት በውጤታማነት ቀጥሎ ተጨማሪ የትግራይ ክልል ከተሞችን ከጁንታው ታጣቂ ነፃ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በዚህም በአድዋ ግንባር የተንቀሳቀሰው ሰራዊት ሃውዜን፣ አብርሃ ወአፅብሃንና ውቅሮን የተቆጣጠረ ሲሆን አጉላን በግማሽ ቀን መቆጣጠሩን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም በመቐለ አቅራቢያ ወደሚገኘው መሰቦ ተራራ እየገሰገሰ ሲሆን ይህም መቐለን በጥቂት ቀናት ውስጥ ለመቆጣጠር እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

በሁለተኛው ግንባርም በአዲግራት በኩል ሳንቀጣ እና አልነጃሺን በመቆጣጠር ውቅሮ ገብቷል ነው ያሉት።

በሶስተኛው የራያ ግንባር ደግሞ አዲቀይህን የተቆጣጠረ ሲሆን ሒዋናን በመቆጣጠር ሁሉንም ምሽጎች ሰባብሮ ወደፊት እየገሰገሰ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በመቐለ ያለውን የወንጀለኛ ቡድን የመቆጣጠር ተግባር በማጠቃላይ ምዕራፍነት የተያዘ ሲሆን ሰራዊቱ ግዳጁን በምን አኳኋን መፈጸም እንዳለበት በቂ ዝግጅት አድርጎ የወንጀለኛውን ቡድን በቁጥጥር ስር ለማዋል መዘጋጀቱን አመልክተዋል።

የትግራይ ህዝብ ሰራዊቱ የጁንታውን አባላት ለመያዝ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ለመከላከያ ሰራዊቱ በተግባር ወገንተኝነቱን ማሳየቱንም አውስተዋል።

ህዝቡ በሰራዊቱ ላይ ጥይት አለመተኮሱን የትግራይ ህዝብና ጁንታው የተለያዩ መሆናቸውን አረጋግጧል ብለዋል።

የጁንታው ቡድንም በፕሮፓጋንዳ ጭምር እያፈገፈገ መሄዱ ሽንፈቱን እያረጋገጠ መሆኑን አመልክተዋል።

በማጠቃለያው ምዕራፍ መቐለን ለመቆጣጠር የሚያስሉ ስትራቴጂክ ቦታዎች መያዙንም አስታውቀዋል።

በራያ በኩልም አድቀይህ ፣ አዲመሳኖን እና ሂዋናን ከታጣቂ ሃይሉ ነፃ ማድረጉን ገልጸዋል።

በጉላን በኩል መንገድ ለመዝጋት ቢሞክርም እንዳልተሳካለትና ወደ ኋላ ማፈግፈጉን ተናግረዋል።

አሁን ላይ መቐለ ብቻ መቅረቱን የገለጹት ሌተናል ጀኔራል ሀሰን በጥቂት ቀናት ወስጥ ተጠናቆ ጁንታው ለህግ እነደሚቀርብ አረጋግጠዋል።

የጁንታው ሃይል በራያ በኩል ያለ የሌለ ሃይሉን በመጠቀም የሰራዊቱን ጥቃት ለመቋቋም ቢሞክርም በመመታቱ ለመልቀቅ ተገዷል ነው ያሉት።

የህወሓት ጁንታ ሽንፈቱን እያረጋገጠ በመምጣቱ በሀሰት ወሬ ላይ ተጠምዶ ህዝብን በማደናገር ላይ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.