Fana: At a Speed of Life!

ሱዳን ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር ለመምከር ልዑኳን ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ላከች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሱዳን ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር ለመምከር ልዑኳን ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መላኳ ተሰምቷል።

ሱዳን ወደ ዱባይ ልዑካንን የላከችው አሜሪካ ለሽብር ድጋፍ ከሚያደርጉ አገራት ዝርዝር ውስጥ ስሟን እንድታወጣ ለመምከር ነው ተብሏል።

ልዑካኑን እየመሩ ወደ ዱባይ ያቀኑት የሱዳን የሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ሌተናል ጄነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሃን መሆናቸውም ታውቋል።

አሜሪካ ሱዳንን ለሽብር ድጋፍ ከሚያደርጉ አገራት ዝርዝር ውስጥ ያካተተችው በአውሮፓውያኑ አቆጣጣር በ1993 እንደነበር ይታወሳል።

ሱዳን በዝርዝሩ ውስጥ የተካተተችው ለታጠቁ ኃይሎች ድጋፍ በማድረግ በሚልና የአልቃይዳ መሪ የነበረው ኦሳማ ቢን ላደን ሱዳን ውስጥ አምስት ዓመታትን በመኖሩ እንደሆነ ይነገራል።

በዚህም አሜሪካ የሽብር ጥቃት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች 300 ሚሊየን ዶላር እንድትከፍል ሱዳንን ጠይቃለች።

ሰሞኑን ደግሞ የመካከለኛ ምስራቅ አገራት ከእስራዔል ጋር ወደ መደበኛ ዲፕሎማሲ እየገቡ ይገኛሉ።

አሜሪካም ሱዳን ከእስራዔል ጋር መደበኛ ዲፕሎማሲ እንድትጀምር እያግባባቻት መሆኑ እየተነገረ ነው።

ከሳምንታት በፊትም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ካርቱም ሄደው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብደላህ ሀምዶክ ጋር መወያየታቸው የሚታወስ ነው።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.