Fana: At a Speed of Life!

ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ጸብ የመፍጠር ዓላማ የላትም” ጠ/ሚ/ር ሀምዶክ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 28 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የሱዳን ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሀምዶክ ከሱዳን ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ሀገራቸው ከጎረቤት ኢትዮጵያ ጋር ጸብ የመፍጠር ዓላማ የላትም ሲሉ ተናገሩ፡፡
 
እንደ አል ዐይን ዘገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄን ያሉት በሱዳን በነበረው የለውጥ እንቅስቃሴ ወቅት የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ሀሰን አልበሽርን ከስልጣን ካወረደ በኋላ ለተቃውሞ አደባባይ የነበሩ ሰልፈኞች ወደ ቤታቸው እንዲገቡ በማስጠንቀቅ በወሰደው እርምጃ በርካታ ሰዎች የተገደሉበትን አንደኛ ዓመት መታሰቢያ በማስመልከት ከብሔራዊ ቴሌቪዥኑ ጋር ባደረጉት ቆይታ ነው፡፡
 
ከኢትዮጵያ ጋር የተያያዘ የተለየ የድንበር ችግር ጉዳይ የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ቀደም ሲልም በተለያዩ ጊዜያት የነበረ ነው ብለዋል፡፡
 
ሱዳን ከተለያዩ ጎረቤት ሀገራት ጋር የድንበር ችግሮች ሲያጋጥሟት እንደነበርም አውስተዋል፡፡
 
“ከኢትዮጵያ ጋር ያለን ግንኙነት በባህል ፣ በታሪክ እና በመልክአ ምድር እና በመልካም ጉርብትና የተሳሰረ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
 
እናም “በመካከላችን የሚፈጠሩ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችሉ ስልቶች አሉን” ብለዋል፡፡
 
በመሆኑም ከሰሞኑ የተፈጠረው ክስተትም በዚህ መንገድ እንደሚፈታ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዶክ ገልጸዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.