Fana: At a Speed of Life!

ሳፋሪኮም እና ሄሊዎስ ታዎርስ በኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎታቸውን ገለፁ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሳፋሪኮም እና ሄሊዎስ ታዎርስ ኢትዮጵያ ለግሉ የቴሌኮም ዘርፍ ያመቻቸችውን እድል ለመጠቀም ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው አስታወቁ።

ሄሊዎስ ታዎርስ የቴሌኮም አቅራቢ መቀመጫውን ለንደን ያደረገ ሲሆን ሳፋሪኮም በበኩሉ ዋና መስሪያ ቤቱን ኬንያ ያደረገ በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ትርፋማ የሆነ ደርጅት ነው።

የሄሊዎስ ታዎርስ የፋይናንስ ሃላፊ ቶም ግሪንውድ ኢትዮጵያ ለድርጅታቸው እጅግ ሳቢ የገበያ መዳረሻ መሆኗን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ገበያ ለመሰማራትም ከአጋሮች ጋር ስምምነት በማድረግ መዘጋጀታቸውንም ነው የገለፁት።

የሳፋሪኮም ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፒተር ንዴግዋ በበኩላቸው ተቋሙ ከአጋሮቹ ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ፍቃድ ለማግኘት ፍላጎት እንዳለው ገልፀዋል።

ዋና ስራ አስፈፃሚው የቴሌኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ በዓለም ላይ የማደግ እድል ካላቸው ኢንዱስትሪዎች አንደኛው መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በተሌኮም ኢንዱስትሪ ተመራጭ ከሆኑ ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ እንደሆነችም ነው ያብራሩት።

በኢትዮጵያ ለመሰማራት ፍላጎታቸውን የገለፁት ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ያላት የህዝብ ቁጥር በሀገሪቱ በቴሌኮም ዘርፍ እንዲሰማሩ ምክንያት እንደሆናቸው አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ሁለት የቴሌኮሙኒኬሽን ፈቃዶችን ለመስጠት የፍላጎት መግለጫ መጠየቂያ ባለፈው መጋቢት ወር አውጥታለች።

ይህም የኢትዮጵያን የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ ለግሉ ዘርፍ የመክፈት ሂደት ዋናው አካል ነው።

ኢትዮ ቴሌኮም ይዞ ከሚገኘው ፈቃድ በተጨማሪ ሁለት ፈቃዶችን በቴሌኮሙኒኬሽን ሥራ ላይ ለተሠማሩ ኩባንያዎች የመሥጠት ሂደት መንግስት በዘርፉ ውድድርን ለመፍጠር ካቀዳቸው የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳዎች አንዱ መሆኑን መንግስት ገልጿል።

 

ምንጭ፡- standardmediaና developingtelecoms

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.