Fana: At a Speed of Life!

ሴቶች በሁሉም ዘርፍ ብቁ እንዲሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና ከፍተኛ ነው – ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 12 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ሴቶች በሁሉም ዘርፍ ብቁ እንዲሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲን ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝታቸውም የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሴት ተማሪዎችን ተሳትፎ በማሳደግ በሀገር ልማት የድርሻውን እንዲወጣ ፕሬዚዳንቷ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሴቶች ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ ብቻ ሳይሆን በስኬት እንዲያጠናቅቁ ማድረግ ይገባል ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፥ ለዚህ ደግሞ የዩኒቨርሲቲዎች አስተዋጽኦ የማይተካ በመሆኑ በመደገፍና በማብቃት በልዩ ትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል ።

የሁሉም ችግሮች ምንጭ ድህነት በመሆኑ መንግስት የህዝቡን ህይወት ለመለወጥ እየሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች የአዳዲስ ሃሳቦች መፍለቂያ እንጂ ትምህርት በሆነ ባልሆነ የሚቋረጥባቸው ሊሆኑ አይገባምም ነው ያሉት።

የጋሞ አባቶች የሰላምና እርቅ መንገድና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሰላማዊ የትምህርት ሂደት ለሚያጋጥሙ ችግሮች ሀገራዊም ሆነ ክልላዊ መፍትሔዎች እንዳሉ የሚያሳዩ ናቸውም ብለዋል።

እንዲሁም የፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት በስድስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሴት ተማሪዎች ማጠናከሪያ ትምህርት ለመስጠት ዝግጅት እንዳጠናቀቀ መግለጻቸውን ከደቡብ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ መላክታል፡፡

በሌላ በኩል ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ እና ሚኒስትሮች በአርባምንጭ ከተማ የሚገኘውን አረንጓዴ ፓርክ ጎብኝተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅን ጨምሮ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳውና ሌሎችም ሴት ከፍተኛ አመራሮች ዛሬ ወደ አርባ ምንጭ ከተማ መግባታቸው ይታወቃል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.