Fana: At a Speed of Life!

ስሁል ሽረ አጠቃላይ ሆስፒታል መድኃኒቶችንና የሕክምና ቁሶችን ከጤና ሚኒስቴር ተረከበ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ስሁል ሽረ አጠቃላይ ሆስፒታል ከጤና ሚኒስቴር የተላከለትን የስኳርና ሌሎች ሕሙማንን ለማከም የሚያስችሉ መድኃኒቶችንና የሕክምና ቁሳቁሶችን ተረከበ።
የህወሓት ጁንታ በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ የፈፀመውን የክህደት ጥቃት ተከትሎ በትግራይ ክልል የተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች ተከስተዋል።
በተለይ የትራንስፖርት እንቅስቃሴው በተቋረጠባቸው ጊዜያት እንደ መድኃኒትና መሰል አስፈላጊ ቁሶችን ወደ ክልሉ ለማስገባት እንቅፋት ገጥሞ እንደነበረ የሚታወቅ ነው።
በዚህ ችግር ውስጥ ከገቡ የጤና ተቋማት መካከል የስሁል ሽረ አጠቃላይ ሆስፒታል አንዱ ሲሆን መድኃኒትና የሕክምና ቁሶች እጥረት በመከሰቱ የጤና ባለሙያዎችና ታካሚዎች ለአንድ ወር ተቸግረው ቆይተዋል።
የሆስፒታሉ ጊዜያዊ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ብርሃነ ተስፋይ እንደገለጹት፤ ላለፈው አንድ ወር ያህል ጊዜ ሆስፒታሉ በተለይ የስኳርና የደም ግፊት ሕሙማንን ለማከም በመድኃኒት እጥረት ምክንያት ችግር ውስጥ ገብቶ ነበር።
አሁን ግን የጤና ሚኒስቴር ለስኳር ሕሙማንና ለሌሎች ታካሚዎች የሚሆኑ መድኃኒቶችን ጨምሮ የሕክምና ቁሶችን ለሆስፒታሉ ማቅረቡን ተናግረዋል።
“የተረከብናቸው መድኃኒቶችና የሕክምና ቁሶች በሞት አፋፍ ላይ ለሚገኙ ሕሙማን ተስፋ፤ ለሕክምና ባለሙያዎች ደግሞ ትልቅ መፍትሄ የሚሰጡ ናቸው” ብለዋል።
ሚኒስቴሩ የላካቸውን ከ2 ሺህ በላይ ብልቃጥ ኢንሱሊን፣ የቲታነስ መድኃኒት፣ የድንገተኛ ህሙማን ማከሚያዎችና የኮሮናቫይረስ መከላከያ ቁሶችን መረከባቸውን ገልጸዋል።
የሽረ ከተማ ጊዜያዊ ከንቲባ መምህር ሀጎስ በርሄ በበኩላቸው ÷በከተማዋ የተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች መከሰታቸውን ጠቁመው፤ በተለይ የመድኃኒት እጥረቱ ፈታኝ እንደነበር ተናግረዋል።
“የሕክምና ቁሶቹ በሚፈለጉበት ጊዜ በመድረሳቸው ለሕሙማኑ እንዲደርስ ተገቢውን ክትትል እናደርጋለን” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.