Fana: At a Speed of Life!

ስዊድን እና ፊንላንድ ኔቶን ለመቀላቀል ማመልከቻ ደብዳቤ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ግንቦት 10፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ስዊድን እና ፊንላንድ ኔቶን የመቀላቀል ጥያቄያቸውን ለኔቶ ዋና ፀሃፊ ጀንስ ስቶልተንበርግ በይፋ በደብዳቤ አቅርበዋል።
በኔቶ ስዊድን እና ፊንላንድን ተወካይ ዲፕሎማቶች ከዋና ፀሃፊው ጄንስ ስቶልተንበርግ ጋር የተገናኙ ሲሆን አገሮቻቸው ኔቶን ለመቀላቀል የፃፈውን ደብበዳቤ ለኔቶ ዋና ፀሃፊ አስረክበዋል፡፡
ዋና ፀሃፊው ጀንስ ስቶልተንበርግ ማመልከቻውን ላቀረቡት ዲፕሎማቶች ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን የሀገራቱ ውሳኔ ለድርጅቱ መስፋፋት ትልቅ አቅም መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ቀደም ሲል ቱርክ ሁለቱን ሀገራት “አሸባሪዎችን ያስተናግዳ፤ ቱርክን ያገለለ የንግድ ሰርዓት አካሄደዋል በማለት የከሰሰች ሲሆን አገራቱ የኔቶ አባል መሆናቸውን በይፋ ተቃውማለች፡፡
በተለይም ሀገራቱ የቱርክ መንግስት አሸባሪ የሚለውን የኩርድ ታጣቂዎችን አላወገዙም፣በተጨማሪም በ2019 በቱርክ የጦር መሳሪያ ግዥ ላይ ማዕቀብ ጥለዋል ስትል ቱርክ ስዊድን እና ፊንላንድን ኮንናለች፡፡
የኔቶ ዋና ኃላፊ ቀደም ሲል ቱርክ ከሰዊድን እና ፊንላንድ ጋር ያላትን ውዝግብ በመፍታት ሀገራቱ ኔቶን እንደሚቀላቀሉ እርግጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ሀገራቱ ኔቶን ለመቀላቀል የኔቶ አባል ሀገራትን ሙሉ ድምፅ ማግኘት የሚጠበቅባቸው እንደሆነና በዚህም መሰረት ቱርክ ስዊድን እና ፊንላንድ አባል እንዳይሆኑ የመቃወም መብት እንዳላት ተጠቁሟል፡፡
ቀደም ሲልም ስቶክሆልም እና ሄልሲንኪ የነበራቸውን አለመግባባት ወደ ጎን በመተው ሩሲያ ዩክሬን ላይ ወታደራዊ ርምጃ መውሰድ ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ በአሜሪካ መራሹ ኔቶ አባል ለመሆን ፍላጎት አሳይተዋል፡፡
ሞስኮ በበኩሏ ሁለቱ ሀገራት የኔቶ አባል ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ ከኔቶ ራሷን ለመከላከል ዝግጅት እንደምታደርግ መግለጿንም አር ቲ ዘግቧል።
የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይፕ ኤርዶኻን በበኩላቸው፥ ቱርክ እንደ ኔቶ አባልነቷ የራሷን ደኅንነትእና የኔቶን ወታደራዊ ጥምረት ሊጎዳ በሚችል ማንኛውም የመስፋፋት ጥያቄ ተቀባይነት የለውም ሲሉ አስታውቀዋል።
ፕሬዚዳንት ኢርዶሃን ዛሬ በአንካራ በተካሄደው የቱርክ የፍትህ እና ልማት ፓርቲ ስብሰባ ላይ የሰዊድንን እና የፊላንድን ኔቶን የመቀላቀል ይፋዊ ጥያቄ አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት ÷ ቱርክ እንደ አንድ የኔቶ አባል ሀገር የራሷንም ሆነ የኔቶን ደህንነት የሚጎዳ የመስፋፋት ጥያቄ ተገቢነት እንደሌለው ሁሉ ሀገራቱ የኔቶ አባል ለመሆን ያቀረቡትን ጥያቄ እንደማይቀበሉት መግለጻቸውን አናዶሉ ዘግቧል፡፡
ቱርክ ዳር ድንበሯን ከአሸባሪ ቡድኖች የመጠበቅ ፍላጎት እንዳላት እና ይሄም ሊከበርላት እንደሚገባ የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ ስዊድን እና ፊንላንድ ለፒኬኬ/ዋይፒጅ አሸባሪዎች ድጋፍ እየሰጡ ኔቶን ለመቀላቀል መፈለግ ተቀባይነት የለውም ሲሉም ጥያቄውን አጣጥለውታል፡፡
አጋሮቻችን የምንከተለውን ፀረ-ሽብር እንቅስቃሴ እንዲገነዘቡ እና ሀሳባችን እንዲደግፉ እንፈልጋለን ሲሉም ተደምጠዋል ፕሬዚዳንት ኤርዶኻን።
ቱርክ የጥምረቱን እንቅስቃሴ በመደገፍ የምትታወቅ ሀገር ብትሆንም ማነኛውንም የጥምረቱ ሀሳብ ያለ ምንም ጥያቄ እና ቅድመ ሁኔታ ትቀበላለች ማለት አይደለም ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፡፡
የሀገራቱ አባል የመሆን ጥያቄም ሆነ የኔቶ የመስፋፋት ጥያቄ ተቀባይነት የሚያገኘው የቱርክ ፍላጎት ከተከበረ ብቻ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
በኔቶ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት አንድ ውሳኔ ተቀባይነት የሚኖረው ሁሉም የጥምረቱ አባል ሀገራት በሙሉ ድምጽ ከተቀበሉት ብቻ እንደሆነ ዘገባው አስታውሷል፡፡
በሚኪያስ አየለና አመለ ደምሰው
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.