Fana: At a Speed of Life!

ሶማሊያ በኬንያ የሚገኙትን አምባሳደሯን በመጥራት የኬንያ አምባሳደር ከሞቃዲሾ እንዲወጡ አዘዘች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 21፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሶማሊያ መንግስት ኬንያ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብታለች በማለት በናይሮቢ ለሚገኙት አምባሳደር መሀመድ አህመድ ኑር ታርዛን ጥሪ አደረገች።

በተመሳሳይ በሶማሊያ የሚገኙት የኬንያ አምባሳደር ሉቃስ ቱምቦ ለምክክር ሶማሊያን ለቀው እንዲወጡም አሳስባለች።

የጁባላንድ የፌደራል አስተዳደር በመስከረም ወር የተደረሰውን የምርጫ ስምምነት እንዲጥስ ኬንያ ጫና እያሳደረች ነው ሲል የሶማሊያ መንግስት ከሷል።

የኬንያ መንግስት በሶማሊያ የውስጥ ጉዳይ በተለይ ከጁባላንድ ጋር ተያያዞ ጣልቃ በመግባቱ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ውሳኔው መተላለፉን የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቋሚ ፀሐፊ መሀመድ አሊ ኑር ገልፀዋል።

በቀጠናው የደህንነት፣ መረጋጋት እና ልማት ላይ እንቅፋት ሊሆን ይችላል ያለውን የኬንያ ጣልቃ ገብነት እንዳሳዘነው የሶማሊያ መንግስት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ኬንያ ከደህንነት እና ቀጠናዊ ፍላጎቷ ጋር በተያያዘ ለጁባላንዱ አስተዳዳሪ አህመድ መሀመድ ኢስላም ድጋፍ እንደምትሰጥ ይነገራል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.