Fana: At a Speed of Life!

ቀደም ሲል የነበሩትን የንግድ ህጎች ማዳበር አስፈላጊ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 17፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ እና የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች በተመራላቸው የንግድ ህግ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከአስረጅዎች ጋር ተወያይተዋል።

የቋሚ ኮሚቴዎቹ ማብራሪያና ግልጸኝነት የሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎችን ከንግድ ሚኒስቴር እና ከጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ለመጡ አስረጂዎች ማቅረባቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመለክታል።

ከቀረቡት ጥያቄዎችና አስተያየቶች መካከልም በረቂቅ የንግድ ህጉ ላይ መካተት ያለባቸው ሀሳቦች፣ ግልጸኝነትና ማብራሪያ የሚሹ ጉዳዮች፣ ሊቃረኑና ሊያከራክሩ የሚችሉ ሃሳቦች፣ ለትርጉም አሻሚ የሆኑ፣ አላስፈላጊ ክፍተት ሊፈጥሩ የሚችሉ እና ውስንነት ባላቸው ሀሳቦች ላይ ማብራሪያ እንዲሰጥበት የቀረቡት በዋነኛነት ይጠቀሳሉ።

የንግድ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል፥ የንግድ ህጉ ለረጅም ጊዜ አስተዋጽፆ ማድረጉን ጠቁመው የሀገሪቱን የንግድ ስርዓት ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን ለማሻሻል፣ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች እንዲሳተፉ ለማድረግ፣ ሀገር በቀል ኢኮኖሚን ለማነቃቃትና የሀገር ውስጥ አቅምን ለማሳደግ የንግድ ህጉን ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

በንግድ ሚኒስቴር ጀኔራል ዳይሬክተር አቶ በላይሁን ይርጋ በበኩላቸው፥ የንግድ ምዝገባ ሂደትን ከማዘመን፣ የጥቅም ግጭትን ከመፍታት፣ የንግድ ወኪል አሰጣጥ እና ሌሎች ጥያቄዎች መነሳታቸው ረቂቁን መልሶ ለማየት አስገድዷል ብለዋል።

በተያያዘም በቀጣይ በንግድ ማሻሻያው ላይ ሰፊ ውይይት እንደሚያስፈልግ እና ህጉ ከፈረንሳይና ከአውሮፓ ሀገራት የይዘት ቅጅ እንደተወሰደ በውይይቱ የተገኙ አባላት ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተዋል::

የንግድ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ መሰረት አባተ፥ ረቂቅ ህጉ ከሰላሳ ዓመት በላይ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ እንደሚሰራና ረጅም ጊዜ ተወስዶ ውይይት መደረጉ ለአዋጁ የተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ መሆኑን እንደሚያሳይም ነው የገለጹት።

በቀጣይም በረቂቅ ህጉ ላይ ሌሎች ተጨማሪ ውይይቶች የሚደረጉ በመሆኑ በዚህ ህግ ረቂቅ ላይ በመሳተፍ የታሪክ አካል ለመሆን ሁለቱም ሴክተሮች በጋራ እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.