Fana: At a Speed of Life!

ቋሚ ኮሚቴው ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን ኮቪድን ለመከላከል በትኩረት መስራት እንደሚገባ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የመስክ ምልከታ ባደረገበት ወቅት ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራው ጎን ለጎን ኮቪድን ለመከላከል በትኩረት መስራት እንዳለበት አሳሰበ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ዩኒቨርሲቲው ትምህርት ከመጀመሩ በፊት መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ኮቪድን መከላከል የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ተመራቂ ተማሪዎችን ተቀብሎ ስራ መጀመሩን እና የተማሪዎች መማሪያ እና መመገቢያ ክፍሎች እንዲሁም ቤተ-መጽሃፍት እና ቤተ ሙከራ ክፍሎች ለተማሪዎች ምቹ መሆናቸውን ተዘዋውሮ ተመልክቷል፡፡
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር ደረጀ እንግዳ ÷ የኮረና ወረርሽኝን በመከላከል ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማሩን ስራ በይፋ መጀመሩን ገልጸዋል።
በቀጣይ ጥር ወርም ከ1 ሺህ 340 በላይ ተማሪዎች ለማስመረቅ ዕቅድ መያዙን አስረድተዋል።
አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው ከስደት ተመላሽ ለሆኑ ዜጎች የለይቶ ማቆያ ማዕከል ሆኖ ሲያገለግል በመቆየቱ በ17 ህንጻዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በመድረሱ ምክንያት ሙሉ ጥገና እየተደረገለት መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።
በሳይንስና ቴክኖሎጅው ዘርፍ ጥልቀት ያለውና አለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ እንዲቻል በ4 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በጀት በግንባታ ሂደት ያሉት 8ቱ የልህቀት ማዕከላት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም በተያዘላቸው ጊዜ እየሄደ መሆኑን እና ለሀገሪቱ የቴክኖሎጅ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ታረቀኝ ብርሀኑ በበኩላቸው÷ በሀገሪቱ የጸጥታ ችግር ምክንያት ብዛታቸው 200 የሚጠጉ ተማሪዎች እንዳልተገኙና ብዙውን ቁጥር የሚይዙት ከትግራይ ክልል መሆኖቸውን ጠቁመው በሚመጡበት ወቅት የክለሳ ትምህርት ተሰጥቷቸው የሚመረቁ መሆኑን ተናግረዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አስተባባሪ አቶ አንድነት ሰብስቤ በበኩላቸው÷ በዩኒቨርሲቲው ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ከጸጥታ አካላት፣ ከማህበረሰቡ እና ከተማሪዎች ህብረት እንዲሁም ከአመራሩ ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሰራር ተገቢና በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት እንደሆነ አስገንዝበዋል።
አክለውም ዩኒቨርሲቲው በግንባታ ሂደት ያሉት 8ቱ የልህቀት ማዕከላት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቅቀው ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ ማድረግና ጎን ለጎን ለሚሰሩ ስራዎችም የበለጠ ጥረት መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል።
አያይዘውም በኦዲት ግኝት፣ በመረጃ አሰጣጥ ግልጸኝነት፣ ኮሮናን በመከላከል ረገድ የማክስ አጠቃቀም እና እርቀትን ከመጠበቅ አኳያ የሚታዩ ውስንነቶች ስላሉ በቀጣይ በትኩረት ሊሰራባቸው እንደሚገባም መጠቆማቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.