Fana: At a Speed of Life!

ቋሚ ኮሚቴው የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ባለስልጣን ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዳልተወጣ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በህዝብ ተወካዮች ምከር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ባለስልጣን በአዋጅ የተሰጠውን ኃላፊነት እና ስልጣን በአግባቡ እንዳልተወጣ ገለጸ፡፡
 
ቋሚ ኮሚቴው የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፈቃድ አሰጣጥ፣ ጥራት እና ቁጥጥርን በተመለከተ የ2012 እና የ2013 በጀት ዓመት በክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ኃላፊዎች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጣ አለመሆኑን ጠቁመው÷ መስሪያ ቤቱ እስከ ሚያዚያ 8 ቀን ድረስ የኦዲት ሪፖርት ማስተካከያ እንዲያቀርብ አሳስበዋል፡፡
 
ትምህርት ሚኒስቴር በትምህርት እና ስልጠና ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ አቅጣጫ መቀመጡንም ሰብሳቢው አስታውሰዋል፡፡
 
የፌዴራል ሥነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን መርምሮ በሁለት ወራት ውስጥ ማቅረብ እንዳለበትም ነው ማሳሰቢያ የተሰጠው ፡፡
 
የፍትህ ሚኒስቴርም ከኦዲት ሪፖርቱ አንፃር በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የወንጀል ምርምራ በማድረግ የሁሉንም አፈጻጸም ሪፖርት በሁለት ወራት ውስጥ ለቋሚ ኮሚቴው እንዲያቀርብ ተጠይቋል፡፡
 
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ወይዘሮ አራሪ ሞሲሳ በበኩላቸው÷ የባስልጣን መስሪያ ቤቱ ኃላፊዎች የኦዲት ሪፖርቱን መነሻ በማድረግ ምላሽ ያልሰጡ መሆኑን ገልጸው፥ የተሰጣቸውን ስልጣንና ኃላፊነት በአግባቡ አልተወጡም ብለዋል፡፡
 
በሌላ በኩል ትውልድን ለመቅረጽም ሆነ ለማበላሸት እድሉ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እጅ ላይ መሆኑ ታውቆ ችግሮች በትብብር እንዲፈቱ ሁለንተናዊ ጥረት መደረግ እንዳለበት ገልጸው÷ ከተቋሙ አመራሮችም ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
 
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ በኩል በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፈቃድ አሰጣጥ፣ ክትትልና ቁጥጥር ረገድ ችግሮች የሚታዩበት መሆኑንም የቋሚ ኮሚቴው አባላት አንስተዋል፡፡
 
በከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ባለስልጣን የትምህርትና ስልጠና ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንዱዓለም አድማሴ በበኩላቸው÷ተቋሙ የሰው ኃይል፣ የአደረጃጀት፣ የተሸከርካሪ እና የቢሮ ችግሮች እንዳሉበት መግለጻቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.