Fana: At a Speed of Life!

በሀላባ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ለጥምቀት በዓል ድምቀት ያደርገው ድጋፍ የሰላም፣ የፍቅርና መልካምነት ተግባር ተምሳሌት ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀላባ ቁሊቶ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ለጥምቀት በዓል ድምቀት ያደርገው ድጋፍ የሰላም፣ የፍቅርና መልካምነት ተግባር ተምሳሌት ነው ተባለ።
በደቡብ ክልል ሀላባ ከተማ ትናንትም ይሁን ዛሬ የሙስሊም በዓላት ሲከበሩ ክርስቲያን ወንድሞቻቸው የደስታቸው ተካፋይ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ። ክርስቲያኑም ማህበረሰብ በተመሳሳይ ለሙስሊሙ ሀይማኖታዊ በዓል ድምቀት ይሰራል።
የሰላም፣ የፍቅርና የመቻቻል ተምሳሌት በሆነችው ሀላባ ቁሊቶ ከተማ የዘንድሮ የጥምቀት በዓል ሲከበርም እንደተለመደው የከተማዋ ኢማሞችና ኡለማዎች በከተማው በሚገኝ አደባባይ ላይ በመሰብሰብ ለጥምቀት ከየአድባራቱ የሚወጡ ታቦታት በደመቀ እና ሰላሙ በተጠበቀ መልኩ ታጅበው እንዲሸኙ የበኩላቸውን የማስተባበር እና የማጀብ ሚና ሲወጡ ውለዋል።
ከሀይማኖት አባቶች ጋርም ያሉትና የአባቶቻቸውን ፈለግ የተከተሉት ሙስሊም ወጣቶችም ህዝበ ክርስቲያኑ የታቦታት ሽኝት እየተደረገ በነበረበት ሰዓት በከተማዋ ኑር መስጅድ አካባቢ የእንኳን በሰላም አደረሳችሁ አቀባበልና መስተንግዶ ሲያደርጉ ውለዋል፡፡
በዚህ ነባር ስነስርዓት ላይ ለክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክትን ያስተላለፉት የሀላባ መስጂደል ኑር ኢማም ሀጂ ዩሱፍ ሁሴን “አባቶቻችን በጋራ በዓላትን ሲያከብሩና ሲተባበሩ በመቆየታቸው እኛ ዛሬ በፍቅርና መተሳሰብ ከተማችንንና አካባቢያችንን ሰላምና አንድነት የሰፈነባት እንድትሆን ማድረግ ችለናልና ነገም ልጆቻችን በፍቅርና አንድነት እንዲኖሩ፣ ሀገራቸውንም እንዲጠብቁ ዛሬ ያለን የሀይማኖት አባቶች ትልቅ ስራ መስራት አለብን” ብለዋል፡፡
በዓሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከበር ህዝበ ሙስሊሙና መላው የሀላባ ነዋሪዎች እያደረጉ የሚገኙት የሰላም፣ የፍቅርና መልካምነት ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ሀጂ ዩሱፍ ሁሴን አሳስበዋል፡፡
መላከ ሀይል ቆሞስ አባ ብርሃነ መስቀል ካሳሁን በበኩላቸው፥ የሙስሊም ወንድሞች ጥምቀት በሰላም እንዲጠናቀቅ ላደረጉት ጉልህ አስተዋፅኦ አድናቆት እንዳላቸው ገልፀው፥ “የሀላባ ኢማመቾችና ኡለማዎች ደግሞ የአባቶቻችንን የመተባበርና ፍቅር ተግባርን ስላስቀጠላችሁ ፈጣሪ ያክብራችሁ” ብለዋል፡፡
በጥላሁን ይልማ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.