Fana: At a Speed of Life!

በሀረሪ ክልል የህግ ታራሚዎች ለማምለጥ ያደረጉት ሙከራ በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡

አዲስ አበባ፣መጋቢት 27፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ)በሀረሪ ክልል የህግ ታራሚዎች ለማምለጥ ያደረጉት ሙከራ በቁጥጥር ስር መዋሉን ኮሚሽነር አለምፀሃይ ታደሰ አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ ማረሚያ ቤት የሚገኙ አንዳንድ የህግ ታራሚዎች ዛሬ ከጠዋቱ 2:00 ሰዓት አካባቢ በማረሚያ ቤቱ ሁከት በመፍጠር በሩን ገንጥለው ለመውጣት መሞከራቸው ተገልጿል፡፡
ሆኖም በማረሚያ ቤቱ የኮሚሽኑ አባላት ከፍተኛ ጥረት ሙከራው ሳይሳካ መክፈሹን ነው የማረሚያ ቤቱ ኮሚሽነር አለምፀሃይ ታደሰ ያስታወቁት፡፡
የማምለጥ ሙከራው ከከፈሸ በኋላ ታራሚዎች በሚያድሩባቸው ክፍሎች በተደረገ ፍተሻ÷ 180 ተንቀሳቃሽ የእጅ ሞባይል ስልኮችና በርካታ የቅድመ ክፍያ ሂሳብ ካርዶች በቁጥጥር መዋላቸውንም ነው የተጠቆመው፡፡
በቁጥጥር ስር የዋሉት እቃዎች እንዲቃጠሉ ከመደረጉም ባለፈ÷የማረሚያ ቤቱን በር ገንጥለው ለመውጣት ምን እንዳነሳሳቸውና ሙከራውን ሲያስተባብሩ የነበሩት አካላት እነማን እንደሆኑ እየተጣራ መሆኑን ኮሚሽነሯ ገልጸዋል ፡፡
የሀረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ጣሰው ቻለው በበኩላቸው ÷በድርጊቱ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ አካላት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተሾመ ኃይሉ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.