Fana: At a Speed of Life!

በሀገሪቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሳቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሀገሪቱ የልብና ደም ቧንቧ እንከንን ጨምሮ ሌሎችም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ በሀገሪቱ የበሽታዎችን መስፋፋት ለመቆጣጠርና ለመከላከል የሚያስችል ስርዓት ለማበጀት ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ  እየመከረ ይገኛል።

በምክክር መድረኩ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ፥ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የጤና ችግር ከመሆን አልፎ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጫና እያሳደሩ ናቸው።

በተለይ የልብና ደም ቧንቧ እንከን፣ ካንሰር፣ ስኳር፣ ደም ግፊት እየተስፋፉ በዚህም ህይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ቁጥር ተላላፊ ከሆኑ በሽታዎች  የላቀ መሆኑን  ተናግረዋል።

ከወዲሁ መቆጣጠርና መከላከል ካልተቻለ በቀጣይ  ሀገሪቱን ለከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ  እንደሚዳርጋት አስታውቀዋል።

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መስፋፋት አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰው  ትኩረት በማጣታቸው እንደሆነ ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል።

በአዳማ ከተማ የተዘጋጀው የምክክር መድረክም እነዚህ በሽታዎች ከወዲሁ ለመቆጣጠርና ለመከላከል ስርዓት ለማበጀት መሆኑን አመልክተዋል።

ከበሽታዎች ውስጥ የልብና ደም ቧንቧ በሽታ ሞትን በማስከተል ቀዳሚ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከል ቡድን መሪ ዶክተር ሙሴ ገብረሚካኤል ናቸው።

በሀገሪቱ በየዓመቱ ከሚመዘገበው ጠቅላላው ሞት ውስጥ 52 በመቶ የሚሆነው ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ ውስጥ የልብና ደም ቧንቧ በሽታ 43 ነጥብ 5 በመቶ ድርሻ አለው ብለዋል።

ዋናው ምክንያት ጤናማ ያልሆነ የአመጋገብ ስርዓት እንደሆነ የጠቆሙት ዶክተር ሙሴ በተለይ በምግብ ውስጥ ጨው ማብዛት፣ በቂ አካላዊ እንቅስቃሴ ያለማድረግ፣ ስጋን ጨምሮ የእንስሳት ውጤቶችን አብዝቶ መመገብ፣ ስኳር የበዛበት ጣፋጭ ምግቦች ማዘውተር፣ አልኮልና ትንቧሆ በዋናነት አጋላጭ መንስኤዎች ናቸው ብለዋል።

የበሽታዎችን መስፋፋት በህክምና መቀነስ እንደማይቻል አመልክተው፤ በዋናነት 50 በመቶ መከላከልና መቆጣጠር የሚቻለው አጋላጭ መንስኤዎች በማተኮር  መስራት ሲቻል መሆኑን አስረድተዋል።

ለዚህም በቂ አካላዊ እንቅስቃሴ ከማድረግና የአመጋገብ ስርዓት ከማሻሻል ባሻገር ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓት ማበጀት ወሳኝ መሆኑን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.