Fana: At a Speed of Life!

በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉትን የመድኃኒት አቅርቦት ችግሮች እንዲወገዱ ዘርፉ የተሻለ የህግ ማእቀፍ ያስፈልገዋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉትን የመድኃኒት አቅርቦት ችግሮች እንዲወገዱ ዘርፉ የተሻለ የህግ ማእቀፍ እንደሚያስፈልገው የጤና ሚኒስትራ ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ።

ሚኒስትሯ ከጤና ማህበራዊ ልማት ባህልና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን የኢትዮጵያ የመድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት የሐዋሳ ቅርንጫፍን የስራ እንቅስቃሴ ዛሬ ጎብኝተዋል።

የመድኃኒት አቅርቦት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ የመድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት የሐዋሳ ቅርንጫፍ ብቻ በግዥ፣ በመንግሥትና በአጋር አካላት በነጻ የሚቀርቡ መድኃኒቶችንና መገልገያ መሳሪያዎችን በማሰራጨት ከ500 በላይ ጤና ተቋማትን እንደሚያስተዳደር ገልጸዋል።

የህግ ማእቀፎችን ማሻሻል ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሯ ፥ በተለይ የመድኃኒት ግዥ እና ሌሎች ማናቸውም እቃዎች የሚገዙበት ተመሳሳይ ህግ መኖሩ በጤና ሴክተሩ ላይ ማነቆ ሆኖ መቆየቱን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የመድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብድቃድር ገልገሎ ፥ የአገልግሎቱ ዋና አላማ ፈዋሽነታቸው የተረጋገጠ መድኃኒቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህበረተሰቡ ማቅረብ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህንን ለማስፈጸም ከተሰጠው ስልጣንና ተግባር አንጻር ውስንነቶች እንዳሉበት ጠቅሰው፥ እነዚህ ማነቆዎች እንዲፈቱ ለመንግሥት ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲቀርብ ቆይቶ በዚህ ዓመት ረቂቅ አዋጁን መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

አሁን ላይ አገልግሎቱ በሁለት መንገድ መድኃኒት ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንደሚያደርግ ያመላከቱት ዶክተር አብድቃድር 70 በመቶ የሚሆነው እንደ ሳንባ ነቀርሳ፣ ወባ፣ ኤች አይቪ እና የቤተሰብ ምጣኔ የመሳሰሉት መድኃኒቶችን በነፃ ተደራሽ እየተደረገ ይገኛል።

ቀሪው ደግሞ ከአንድ ጤና ተቋም ከሚቀርበው የመድኃኒት ፍላጎትና ጥያቄ መሠረት በማድረግ ከውጭ ሀገር በግዥ እንደሚሰራጭ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.