Fana: At a Speed of Life!

በህንድ የኢትዮጵያን ኢንቨስትመንት፣ ንግድና ቱሪዝም መስኮች የሚያስተዋውቅ ፎረም ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በህንድ በማድህያ ፕራዴሽ ግዛት ዋና ከተማ ቦህፓል የኢትዮጵያን ኢንቨስትመንት፣ ንግድና ቱሪዝም መስኮች የሚያስተዋውቅ ፎረም ተካሄደ።

በኒውዴልሂ የሚገኘው የኢፌዴሪ ኤምባሲ ከማድህያ ፕራዴሽ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ነው ፎረሙን ያካሄደው።

በፎረሙ ላይ ከ25 በላይ የመድሃኒትና የህክምና መሳሪያዎች አምራቾች፣ በኤሌክትሪክ ዕቃዎች፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች፣ በማሸጊያ ምርት መስኮች ላይ የተሰማሩ የፌዴሬሽኑ አባላት ተሳትፈዋል።

በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ትዝታ ሙሉጌታ፥ ፎረሙ በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት፣ ንግድና ቱሪዝም ዕድሎች ለማድህያ ፕራዴሽ ባለሃብቶች በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና እስያ መተላለፊያ ላይ መገኘቷ የተለየ መልክዓ ምድራዊ ብልጫ እንደሚሰጣትም አንስተዋል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ ከ500 በላይ የህንድ ባለሃብቶች በተለያዩ መስኮች በመሰማራት መዋዕለ ነዋያቸውን ማፍሰሳቸውን ጠቅሰው፥ ይህም ኢትዮጵያ ለህንድ ባለሃብቶች ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለመሆኗ ማሳያ ነው ብለዋል።

የማድህያ ፕራዴሽ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ዶክተር ራድሃ ሻራን፥ ግዛቱ ካለው ሃብት አንፃር የኢንቨስትመንትና ንግድ ምንጭ ሊሆን እንደሚችል አብራርተዋል።

በግዛቱ በርካታ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ያሟሉ የመድሃኒትና የህክምና መሳሪያዎች፣ የኤሌክትሪክ ዕቃዎች፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ ምርቶች፣ የማሸጊያ ማምረቻዎች እንደሚገኙ መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.