Fana: At a Speed of Life!

በህወሓት ቀንበር ስር ያለው የትግራይ ህዝብ በከፋ ባርነት ውስጥ እንደሚገኝ በቅርቡ አምልጠው የመጡት የቀድሞ የስራ ሀላፊ ተናገሩ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት የትግራይ ህዝብን በማፈን ክልሉ በከፋ ባርነት ውስጥ እንዲኖር አድርጓል ሲሉ በቅርቡ ከትግራይ ክልል አምልጠው ወደ አማራ ክልል የገቡት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አባል እና የቀድሞ የሰሜን ምዕራብ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር የማነ ሃይለ ገለጹ፡፡

 

ኢንጂነር የማነ የፌደራል መንግስት ባለፈው ሰኔ ወር 2013 ዓ.ም ለትግራይ ህዝብ የጥሞና ጊዜ በመስጠት ከመቀሌ ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ክልሉን የተቆጣጠረው አሸባሪው ህወሓት የጊዜያዊ አስተዳደር በነበሩ አባላት ላይ በርካታ ግፎች መፈጸሙን አስታውሰዋል፡፡

 

አሸባሪው ህወሓት የትግራይ ህዝብ ፈርቶት እንዲኖር፣ ሞራል እንዲያጣ እና የክልሉ ወጣቶች ባላቸው እውቀት ህዝብን እንዳያገለግሉ ከማሰብ የሚመነጭ የማፈን እና ሌሎች ዘግናኝ ግፎችን እየፈጸመ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

 

ከዚህ ባለፈም የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር  አባላት በነበሩት አመራሮች እና ግለሰቦች ላይ የተጠና ግድያ መፈጸማቸውን ነው የገለጹት፡፡

 

ለዚህ ዕኩይ ተግባሩም ሲቪል መስለው የሚንቀሳቀሱ ገዳይ ቡድኖችን ማሰማራቱን ጠቁመው፥ እሳቸውም ከዚህ ቡድኑ ግድያ ማምለጣቸውን ተናግረዋል፡፡

 

የትግራይ ህዝብ ከተቀረው  ወንድም የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲነጠል  መደረጉን የገለጹት ኢንጂነር የማነ፥ አሸባሪው ህወሓት “አራት ኪሎ እገባለሁ” በሚል አይኑን ጨፍኖ በአማራ እና አፋር ክልሎች በለኮሰው ጦርነት የትግራይ ከተሞች በጦርነቱ ምክንያት አካላቸው የጎደሉ ወጣቶች መኖሪያ ማዕከል ሆነዋል ብለዋል፡፡

 

በዚህ ሳቢያም አዲግራት፣ ሽረ እና አክሱም ከተሞች በቁስለኛ እና አካላ ጉዳተኛ ወጣቶች የተሞሉ ከተሞች መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

 

በጦርነቱ ከፍተኛ  የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ወጣቶችም መቀሌ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እና ሆስፒታሎች እንደሚገኙ ነው ያብራሩት፡፡

 

በጦርነቱ ወጣቶች ላይ የደረሰው  የአካል ጉዳት እጅግ የሚዘገንን  መሆኑን በመግለጽ፥ የተጎጂ ቤተሰቦች  ከፍተኛ ስቃይ እና ሀዘን ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

 

ስለሆነም በአሸባሪ ህወሓት አገዛዝ የተማረረው ህዝብ ህይወቱን ለማዳን ሲል ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ወደ አጎራባች ክልሎች እያመለጠ እንደሚገኝ ነው ኢንጂነር የማነ የተናገሩት፡፡

 

ይሁን እንጂ ከክልሉ ወጥተው ወደ አጎራባች ክልሎች የሚፈናቀሉ ዜጎችን የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች  መንገድ ላይ በማገት ችግር እየፈጠሩባቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

 

በዚህም የተፈናቃዮችን ንብረት እና ገንዘብ ከመዝረፍ ባለፈ ሴቶችን በመድፈር፣ ገንዘብ ከሌላቸውም ወደ መጡበት  መልሰው በማሰር እንግልት እያደረሱባቸው መሆኑን አብራርተዋል፡፡

 

በአንጻሩ ከአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች እገታ አልፈው ወደ አማራ ክልል ለመግባት እድሉን ያገኙ ተፈናቃዮች በክልሉ በሚገኙ የጸጥታ አካላት መልካም አቀባበል እየተደረገላቸው መሆኑን አውስተዋል ።

 

አሁን ላይም በአሸባሪው ህወሓት ቡድን ቁጥጥር ስር የሚገኘው የትግራይ ክልል ህዝብ በከፍተኛ ባርነት ውስጥ ይገኛል ሲሉ ነው ኢንጂነር የማነ ያስገነዘቡት፡፡

 

 

በሜሮን ፉፋ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.